ትምህርትን በጉልበት፣ በገንዘብ እና በሃሳብ መደገፍ፦

2
ባሕር ዳር: መስከረም 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳድር የዝቋላ ወረዳ የኅብረተሰብ ክፍሎች ትምህርትን በጉልበት፣ በሃሳብ እና በገንዘብ እየደገፉ እንደሚገኙ የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
ተማሪዎችም ክልሉ ገጥሞት በነበረው ጸጥታ ችግር ምክንያት አቋርጠው የነበረውን ትምህርት መቀጠላቸውን ለአሚኮ ገልጸዋል።
እስከዳር መብርህቱ በ2016 የትምህርት ዘመን በዝቋላ ወረዳ የጽጽቃ ትምህርት ቤት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እንደነበረች ተናግራለች፡፡
ተማሪዋ በአካባቢው በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ትምህርቷን አቋርጣ ያለ ዕድሜዋ ለመዳር ዝግጅት ላይ እንደነበረች አልሸሸገችም፡፡
ተማሪዋ ልትዳር መኾኗን የሰሙ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች እና መምህራን ወላጅ አባቷን በመገሰጻቸው የጋብቻ ሂደቱ መቋረጡን ተናግራለች።
ተማሪ እስከዳር በ2018 የትምህርት ዘመን ያቋረጠችውን ትምህርት ለመቀጠል መመዝገቧን ጠቁማለች፡፡
የዝቋላ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የጸዳው ገላው በወረዳው በሚገኙት 15 ቀበሌዎች የተማሪዎች ምዝገባው ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ የትምህርት መሪዎች፣ የቀበሌ የሥራ ኀላፊዎች፣ የወረዳ አሥተባባሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት የ2017 የትምህርት አፈጻጸም መገምገሙን ተናግረዋል፡፡
በግምገማውም ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ጥሩ አፈጻጻም መመዝገቡ ተመላክቷል ነው ያሉት። በአንጻሩ ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ባሉት የትምህርት እርከኖች ድክመት ታይቷል ብለዋል።
ያለፈውን የትምህርት ዘመን ግምገማ መሰረት በማድረግም የ2018 የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ መኾኑን ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
በወረዳው ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የሚያስተምሩ 28 ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ ያሉት ኀላፊው 19 ሺህ 333 ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዷል፡፡ ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም 17 ሺህ 443 ተማሪዎችን በመመዝገብ የዕቅዱን ከ90 በመቶ በላይ ተመዝግቧል፡፡
የቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን የዕቅዱን ከመቶ በላይ ተከናዎኗል፤ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ምዝገባም እየተካሄደ መኾኑን ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
የሁለተኛ ደረጃን በተመለከተም 4 ሺህ 557 ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ 1 ሺህ 912 ብቻ በመመዝገብ አፈጻጸሙን ከ50 በመቶ በታች ያደርገዋል፡፡
ወረዳው ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ
በጸጥታ ችግር ውስጥ የነበረ በመኾኑ በርካታ ትምህርት ቤቶች እስከ ግብዓታቸው በመውደማቸው አያሌ ተማሪዎች ተፈናቅለው እንደነበር ኀላፊው አስታውሰዋል፡፡
በተለይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የቤተ ሙከራ ክፍላቸውን መልሶ የማቋቋም ሥራው ዝቅተኛ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠው ያለዕድሜአቸው ወደ ትዳር እንዲገቡ፣ ለስደት እንዲዳረጉ፣ ወደ ተለያዩ ቦታዎች እንዲሰደዱ ማድረጉን አቶ የጸደው ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም
አለ ያሉት ኀላፊው በሁሉም ትምህርት ቤቶች ምዝገባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ወላጆችም ልጆቻቸውን በማስመዝገብ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
ኅበረተሰቡ በጉልበት፣ በሀሳብ እና በገንዘብ ትምህርትን እየደገፈ እንደሚገኝ ነው የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የተናገሩት፡፡ ግብዓትም ለትምህርት ቤቶች መሰራጨቱን ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
በወረዳው የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ በመጠገን ረገድ ረጂ ድርጅቶች ከመንግሥት እና ከኅብረተሰቡ ጎን እንዲሰለፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ፍታለሽ ምኅረቴ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ263 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ምዝገባው እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የ2018 የትምህርት ዘመን ትምህርትን ለመጀመርም አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን ምክትል ኀላፊዋ ጠቁመዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በትምህርት ዘመኑ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ መታቀዱን ነው የገለጹት። ለዚህም በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።
ቢሮ ኀላፊዋ በትምህርት ጉዳይ ላይ አሁን የተፈጠረው የማኅበረሰቡ ቁጭት፣ የአጋር አካላት ድጋፍ እና በየደረጃው ያለው ቅድመ ዝግጅት የታቀደውን ውጤት ለማሳካት አቅም ይኾናልም ብለዋል።
የዚህ ዓመት የመማር ማስተማር ሥራም መስከረም 05/2018 ዓ.ም እንደሚጀምር የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleተግዳሮቶችን በመሻገር የሀገር ዕድገትን የሚያፋጥኑ ሥራዎችን መሥራት ይገባል።