ተግዳሮቶችን በመሻገር የሀገር ዕድገትን የሚያፋጥኑ ሥራዎችን መሥራት ይገባል።

1
ጎንደር: መስከረም 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በከተማዋ ለሚገኙ መሪዎች ሥልጠና እየሰጠ ነው።
የከተማ አሥተዳደሩ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት ለመሪዎቹ የሚሰጠው ሥልጠና ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ሦሥት ቀናት ነው የሚቆየው።
ሥልጠናው የብልጽግና ፓርቲ ያለፉት ዓመታት ስኬት እና ያጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም ፓርቲው ሊተገብራቸው በሚችሉ የቀጣይ ትኩረቶች ላይ ያተኮረ ነው።
በመድረኩ ላይ የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፣ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ መኮንን እና ሌሎችም የከተማዋ ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
ተግዳሮቶችን በመሻገር የሀገር ዕድገትን የሚያፋጥኑ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ መኮንን ገልጸዋል።
መሪዎች ለልማት ሥራዎች እንቅፋት የኾኑ አሠራሮችን በማስተካከል ለዜጎች ምቹ ሀገር መፍጠር እና ዴሞክራሲን ለማስፈን በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያን ካደጉ ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ በትኩረት የሚሠራ ፓርቲ መኾኑን ያነሱት አቶ ተስፋ አግላይ የፓለቲካ ሥርዓትን በማስወገድ የሀገር ዕድገትን ወደፊት ሊያራምድ የሚችል የፖለቲካ ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።
በሀገሪቱ እየተፈጠሩ የሚገኙ የሰላም እጦት ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ መሪዎች ቁርጠኛ መኾን እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመረዳት የሀገርን ዕድገት የሚያሳልጡ ተግባራትን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት የከተማዋን ሁለንተናዊ ዕድገት እና የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው፤ በየደረጃው የሚገኙ ሁሉም መሪዎችም በዚሁ ተግባር ላይ እኩል የሚተጉ መኾን እንደሚገባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ደስታ ካሳ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleትላልቅ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማሳካት መጭውን ጊዜ አስቦ መሥራት ይገባል።
Next articleትምህርትን በጉልበት፣ በገንዘብ እና በሃሳብ መደገፍ፦