
ባሕር ዳር: መስከረም 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከአምስቱ የኢኮኖሚ አውታሮች ውስጥ አንዱ የኾነው ቱሪዝም ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ነው። ቱሪዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ እጅግ ከፍተኛ ነው። በተለይ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ዕድገት ውስጥ መልካም ተጽዕኖ ያለው ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን በ2019 ላይ ቢቢሲ ይዞት የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ቱሪዝም ከአጠቃላይ የዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ የነበረው ድርሻ 10 በመቶ እንደነበር ያትታል። ይህ ይዘት የሚያመለክተው ቱሪዝም በኢኮኖሚው ዘርፍ ምን ያህል ሚዛን መድፋት የሚችል መኾኑን የሚያሳይ ነው።
በዘርፉ የጸጋው ባለቤት እንደኾነች የሚነገርላት ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም ለቱሪዝም መዳረሻዎች ትኩረት ሰጥታ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች። ያለፈው ዓመት በርካታ ጎብኝዎችን ሊስቡ የሚችሉ ተግባራት ሲከወኑበት የቆየ ዓመት ነበር ማለት ይቻላል። የኮሪደር ልማቶች፣ የሙዚየም እድሳቶች እና ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ከልማቶች ውስጥ ተጠቃሽ ነበሩ።
ባለፈው ዓመት የደሴ ሙዚየም ስር ነቀል እድሳት ከተደረገላቸው የቱሪዝም መዳረሻዎች ውስጥ አንዱ ነው።
የደሴ ሙዚየም በ1909 ዓ.ም በደጃዝማች ዮሴፍ ብሩ ለመኖሪያ ቤት አገልግሎት የተገነባ ሲኾን ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በሙዚየምነት እያገለገለ የቆዬ ታሪካዊ የሀገር ሃብት ነው።
ሙዚየሙ የወሎ አካባቢ ማኅበረሰብን እሴት፣ ባሕል እና ቅርስ ይዞ ቆይቷል። በ1973 ዓ.ም በወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት በነበሩት በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዘመን ሥራ እንደጀመረም ይነገራል።
የሙዚየሙ ታሪካዊ ሕንጻ 12 ሺህ 565 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲኾን በ22 ክፍሎች የተደራጁ ባሕላዊ እና ታሪካዊ ቅርሶችንም የያዘ ነው።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ትዕግስት አበበ በ2017 በጀት ዓመት የቱሪዝም ዘርፉን በማልማት እና በማጎልበት በኩል ሰፋፊ ሥራዎች የተከናወኑበት ዓመት ነበር ብለዋል።
ከተሠሩ ዐቢይ ተግባራት ውስጥ በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ደርሶበት የነበረው እና አገልግሎት አቁሞ የነበረው የደሴ ሙዚየም ዋናው እንደኾነም ገልጸዋል።
የደሴ ሙዚየም ከብሔራዊ ሙዚየም ቀጥሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ በቅርስ ስብስቡም ኾነ በነባርነት ቀዳሚ ሊባል የሚችል የሀገር ሃብት እንደኾነ ተናግረዋል። በ2017 በበጀት ዓመት የነበረውን ቅርጽ በጠበቀ መልኩ ግብረ ሕንጻውን የማደስ ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት።
ከቅርስ ባለሥልጣን ባለሙያዎች ጋር በጋራ ነባር ይዘቱ እንዲመለስ የማድረግ ተግባር እና በውስጡ ያሉ ቅርሶች ቀጣይነታቸው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የማድረግ ተግባር ተከናውኗል ነው ያሉት።
ዕድሳቱን ለማከናወን ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደፈጀም መምሪያ ኀላፊዋ ገልጸዋል። ወጭው ደግሞ የቅርስ ባላደራ፣ የፌዴራል ቅርስ ባለሥልጣን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ ከብሪትሽ ካውንስል ጋር በመነጋገር የተከናወነ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
በቀጣይ የደሴ ሙዚየም በዚህ መልኩ መታደሱ የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ረገድ ድርሻው ከፍተኛ ነው ብለዋል። የመዳረሻዎች መልማት ለጎብኝዎች ቁጥር መጨመር ወሳኝ ምክንያት በመኾኑ ቱሪዝሙን በሚገባ ያግዛል ነው ያሉት።
ቱሪዝም ለአንድ ሀገር ዕድገት መሠረት ነው የሚሉት ወይዘሮ ትዕግስት ቱሪዝምን ማበልጸግ እና ከዚህም በላይ ትኩረት ሊሠጠው የሚገባ ዘርፍ ነው ብለዋል።
የቱሪዝም ዘርፍ በትኩረት ከተሠራበት ኢኮኖሚውን በሚገባ መደገፍ የሚችል እንደኾነም ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን