
ባሕር ዳር፡ መስከረም 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ትምህርት ቤቶችን በመገንባት እና በመጠገን እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። በምሥራቅ ጎጃም ዞንም ማኅበሩ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑን የዞኑ አልማ ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አሳውቋል።
የዞኑ አልማ ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙሉ ጥጋቡ እንደገለጹት አልማ በ2018 በጀት ዓመት ከትምህርት በዞኑ 309 የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች መማሪያ ክፍሎችን ለመገንባት አቅዷል።
ለዚህ ፕሮጀክት ደግሞ ወደ 480 ሚሊዮን አካባቢ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ኀላፊዋ ገልጸዋል። ይህንን ሃብት ከማኅበረሰቡ፣ ከአጋር አካላት፣ ከደጋፊዎች፣ ከተቋማት እና ከአጠቃላይ አባሉ ሃብት በማሰባሰብ ለመሥራት እየተንቀሳቀሱ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
የ2018 የትምህርት ዘመን ከመጀመሩ በፊት በቅድመ ዝግጅት ተግባራቸው የተከናወኑ ተግባራትን ሲገልጹም በ2017 ዓ.ም ተሠርተው ዝግጁ ያደረጓቸው እና ያለፈው ሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም ያስመረቋቸው በርካታ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ከመጠገን አኳያ አልማ ከመንግሥት ጋር ኾኖ በምን አግባብ የተጎዱትን ትምህርት ቤቶች ማስተካከል እንደሚቻል ተሳትፎ ያደርጋልም ብለዋል።
ጥቂት ቦታዎች ላይ ፕሮጀክቶች የመቆም አዝማሚያዎች አሳይተው እንደነበር እና አሁንም የቆሙ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል። ፕሮጀክቶች የቆሙበት ምክንያት ግን የጸጥታ ችግሩ ነው ወይስ እኛ ደፍረን ባለመሄዳችን ነው የሚለው ሌላ ጉዳይ ነውም ብለዋል።
ሃብት ከማሰባሰብ አኳያ ውስንነት በመኖሩ የታቀደውን እቅድ ያለማሳካት ችግር እንዳለም ገልጸዋል። በክልሉም ኾነ ከክልሉ ውጭ ያለ የማኅበሩ ደጋፊ እና አባል ባለው አቅም እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን በበኩላቸው በአማራ ክልል የሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ናቸው ብለዋል። ከዚህ አኳያ አልማ በፍትሐዊነት የሚሠራቸው ሥራዎች በርካታ ናቸው ብለዋል።
አልማ ከኅብረተሰቡ ሃብት እያሰባሰበ ኅብረተሰቡ በራስ አቅም ትምህርት ቤቶችን መገንባት እና ከችግር መውጣት እንደሚችል እያሳየ ያለ ተቋም መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ በፊት አልማ የአንደኛ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ሲገነባ እና ሲያስፋፋ መቆየቱንም አስታውሰዋል። በ2018 ዓ.ም ደግሞ በአዲሱ ስትራቴጂክ ዕቅድ መሰረት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል። አልማም በዚህ ረገድ ጥሩ እገዛ እያደረገ መኾኑን ጠቅሰዋል።
እንደ አማራ ክልል በ2018 ዓ.ም አልማ እና ሌሎች አጋር አካሎች ጋር በጋራ በመኾን ከ4 ሺህ በላይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት መታሰቡንም ጠቅሰዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ በተፈጠሩ ሁነቶች የትምህርት ሥራ መደናቀፍ እና የተማረ ትውልድ የማስቀጠል ክፍተት ተፈጥሯል ብለዋል።
በዚህ ረገድ መላው የክልሉ ነዋሪዎች፣ በሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያውያን እና ረጅ ድርጅቶች፣ ሁሉም በትብብር ትውልድ የመታደግ ሥራ ላይ እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!