ሥልጠናው የተሳኩ ሥራዎችን በትክክል ለማስገንዘብ ይረዳል።

2
ባሕር ዳር፡ መስከረም 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት የብልጽግና ፓርቲ ያለፉት ዓመታት የትኩረት መስኮች ላይ ለመካከለኛ እና ዝቅተኛ መሪዎች ሥልጠና እየሰጠ ነው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባለፉት ዓመታት ታቅደው የተሳኩ ሥራዎችን ሕዝብ በትክክል እንዲረዳቸው እና ዕውቅና እንዲቸራቸው መድረኩ አይነተኛ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
በቀጣይም በሚሠሩ ተግባራት ዙሪያ በመወያዬት ሃሳብ አዋጥቶ የጋራ ለማድረግ የመድረኩ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል።
ሥልጠናው ከፍ ያለ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከዚህ የሚገኝን ግብዓት በመያዝ ሕዝቡን እና የመንግሥት ሠራተኛውን በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ዙሪያ ማወያየትም ይገባል ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ጊዜው ታከለ ብልጽግና ፓርቲ በየጊዜው ንደፈ ሃሳባዊ ሰነዶችን በማዘጋጀት መሪዎችን፣ አባላትን እና ማኀበረሰቡን በእሳቤዎች ዙሪያ እንደሚያወያይ አስታውሰዋል።
ፓርቲው በጋራ ታቅደው እና ተሠርተው የመጡ ውጤቶችንም ግንዛቤ ያስጨብጣል ነው ያሉት።
ብልጽግና ፓርቲ ወደፊት ሊሠራቸው የሚያስባቸውን ተግባራት ገቢራዊ ለማድረግ የፖለቲካ እና የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱንም አስታውሰዋል።
በመድረኩ ከጅኦ ስትራቴጂክ ኩስመና ወደ ታደሠ ቁመና እና በብልጽግና የአምስት ዓመታት ሥራዎች ዙሪያ ጥልቅ ውይይት እንደሚካሄድም ተናግረዋል። ሥልጠናው እስከ መስከረም 4/2018 ዓ.ም ይዘልቃልም ነው የተባለው።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleመድኃኒትን ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መውሰድ ምን ሊያስከትል ይችላል ?
Next articleአጋር አካላት ትውልድ የመታደግ ሥራ ላይ እንዲያግዙ ጥሪ ቀረበ።