
ባሕር ዳር: መስከረም 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አንተ ግን ዕለታትን በኃይልህ ትገዛቸዋለህ፤ አንተ ግን ዘመናትን በቸርነትህ ታቀዳጃለህ፤ አንተ ግን በጥበብህ ትጠብቃለህ፤ በቸርነትህም ታኖራለህ፤ ዕድሜን ትጨምራለህ። አንተ ግን ዘመናትን ትሠጣለህ፤ ጸጋንም ታድላለህ። አንተ ግን በረከት እና ረድኤትንም ታበዛለህ።
መባርቅቱን አሳለፍካቸው፤ ማዕበላቱንም አቀለልካቸው፤ ምድር ማዕበል እንዳያስጨንቃት ጠበካት፤ ሰብሏ በበረዶ እንዳይጠፋ በቸርነትህ ጋረድካት፤ አዝዕርትን አበቀልካቸው፤ አብቅለህም እንዲያጎጡ አደረካቸው፤ እነኾም አበባን ሰጠኻቸው፤ ምድርን ባማረ ውበት ከበብካት፤ በሰው እጅ ያልተሠራውን መጎናጸፊያ አለበስካት፤ አብዝተህም አስዋብካት።
ተራራዎችን ሞሸርካቸው፤ በተዋበ ቀለም አስጌጥካቸው፤ እነኾ አፍላጋቱ ባዘቶ መምሰል ጀምረዋል። እነኾ በቸርነትህ አዲስ ዘመንን ሰጥተሃል፤ ክረምቱን አሳልፈሃል፤ የተዋበውን ጊዜም አድለሃል።
ምድርን ጐበኘሃት አጠጣሃትም፤ ብልጽግናዋንም እጅግ አበዛህ፤ የእግዚአብሔርን ወንዝ ውኃን የተመላ ነው፤ ምግባቸውን አዘጋጀህ እንዲሁ ታሰናዳለህና። ትልምዋን ታረካለህ፤ ቦይዋንም ታስተካክላለህ፤ በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ፤ ቡቃያዋንም ትባርካለህ። በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፤ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል።
የምድረ በዳ ተራራዎች ይረካሉ፤ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ፤ ማሰማርያዎች መንጎችን ለበሱ፤ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ፤ በደስታ ይጮኻሉ ይዘምራሉ ተብሎ እንደተጻፈ አንተ በቸርነትህ ዘመናትን ሰጥተሃል። ደስታም ኾኗል።
ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዘመን በቸርነት ተሰጥተዋል፤ ዘመንን አሳልፈው ዘመንን ጀምረዋል፤ በአዲስ ዘመንም አዲስ ነገርን ተስፋ አድርገዋል። በአዲስ ዘመን አዲስ ተስፋ አለና። አዲስ ራዕይ አለና። በአዲስ ዘመን መልካም ነገር ሁሉ ይጠበቃል። ያለፈውም የክፉ ጊዜ ይረሳልና።
በርእሰ አድባራት ወ ገዳማት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም የአራቱ ጉባዔያት መምህር ርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ እግዚአብሔር በዚህ ምድር ከሰጠን ትልቅ ነገሮች አንደኛው ጊዜ ነው፤ እግዚአብሔር የሰጠንን ጊዜን ማንንም ሊሰጠን አይቻለውም፤ እርሱ የሰጠንን ጸጋ ማንንም አልሰጠንም ይላሉ።
እግዚአብሔር ዘመን ሳይፈጠር ነበረ፤ ዘመንን ፈጥሮም አለ፤ ዘመናትን አሳልፎም ይኖራል፤ ዘመናትን ይወስናቸዋል እንጂ ዘመናት አይወስኑትም። እርሱ ግን ዘመናትን በቸርነቱ ይሰጣል፤ አዲስ ዘመንንም ያጎናጽፋል።
ዓለም የተፈጠረችው በጊዜ ነው። እግዚአብሔር ዓለምን በጊዜ ፈጠረ። በጊዜም የሌለ ነገርን አመጣ። ጊዜን የሚጠቀም ሁሉ የሌለ ነገርን ያመጣል። ጊዜውን የማይጠቀም ግን ሕልሙን ታቅፎት ይሞታል። አምላክ በጊዜው ምስጢሩን ገለጠ። በጊዜ የተገባውን ፈጸመ። ጥበበኛ ሰው ማለትም በጊዜው ነገርን የሚፈጽም ነው ይላሉ ሊቁ።
አበው ጊዜያቸውን ተጠቅመዋልና መልካም ነገርን ሠርተዋል። ጊዜን ያልተጠቀመ ሰው ግን በቸርነት የተሰጠች ጊዜው በዋዛ ታልፍበታለች። የምህረት ጊዜን ያልተጠቀመ ሰው መከራ ይታዘዝበታል። እግዚአብሔር ጊዜን የሚሰጠው ለቸርነት ነው። በቸርነት በተሰጠ ጊዜም ቸርነትን ማድረግ የተገባ ነው ይላሉ። አባ እንደሚሉት ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ የሌለው እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር የለም።
ያለ ስስት ዘመናትን መስጠት እንደምን ያለ ቸርነት ነው? ሁልጊዜ ትህትናን ማድረግ እንደምን ያለ ትህትና ነው? ሁልጊዜ መልካሙ ነገር መስጠትስ እንደምን ያለ መልካምነት ነው? ሁልጊዜ ደግነትን ማድረግ እንደምን ያለ ደግነት ነው ?
ማነው የተሰጠውን ዘመን የተጠቀመበት? ማነው በቸርነት የተሰጠውን ጊዜ በጎ ሥራ የሠራበት? ማነው በነጻ የተሰጠውን ዘመን አመስግኖ የተቀበለ?
በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የአራቱ ጉባዔያት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ዘመን በሰዎች ምግባር ይገለጣል፤ ሰው ክፉ በሠራ ጊዜ ዘመኑ በክፉ ሥራ ይጠራል፤ ዓመተ ፍዳ እየተባለ የሚጠራው ዘመን በሰዎች የመጣ እንጂ ዘመኑ ምንም አላደረገም፤ ሰዎች ሀጥያት ሠሩ፤ በሀጥያታቸውም ተቀጡ፤ ያም ዘመን ዓመተ ፍዳ ዓመተ ኩነኔ እየተባለ ይጠራል ይላሉ።
ሰው ሁሉ ክፋት የሚሠራበት ሁሉ የክፋት ዘመን፤ የጦርነት ዘመን ይባላል፤ ሰው በሠራው ሥራ ዘመኑ ክፉ ዘመን ይባላል ነው የሚሉት። ይህም እንዳይኾን ሰው ባለበት ዘመን ሁሉ መልካም ሊሠራበት ይገባል፤ ሰው እድሜው ይነስም ይብዛም ጥሩ ከሠራበት ያ ዘመን መልካም ዘመን ተብሎ ይጠራል። ዘመናችን መልካም ይኾን ዘንድ በዘመናችን መልካም እናድርግ ይላሉ።
የመለሰበት፤ የሰው ልጅም ምህረት ያገኘበት ነውና የምህረት ዘመን ይሰኛል ነው የሚሉት። በቸርነት በተገኘው ዘመን ምድረ በዳ ጠል ያገኛሉ። ምድርም ደስታን ታገኛለች።
ይህ ዘመን የእግዚአብሔር ዓመት ነው። ምህረት የተደረገበት ዘመን ነውና ዓመተ ምህረት ይባላል። አምላክ ምህረትን አድርጓል። በዓመተ ምህረት የሚኖሩትስ ርህራሄን ያደርጋሉንን? ይህን ካላደረጉስ ዘመናቸው ዋጋ የላትም ይላሉ።
በዓመተ ምህረት የሚኖር ሁሉ መገዳደልን፣ ጥልን፣ ግጭትን ያርቅ። የቅድስና ሥራን ይሥራ። ምህረትን ያድርግ። መልካም ግብርም ይፈጽም ነው የሚሉት።
ሰው ቅዱስ ሁኖ ዘመኑን እንዲቀድስ ሥልጣን ተሰጥቶታል። ይህም በእግዚአብሔር ፊት የተወደደ ነው። እኛም ይህችን ዓመት እንቀድሳት። ይህችን ዓመት እናክብራት ነው የሚሉት። ሰው ቅዱስ ሲኾን ዘመኑ ቅዱስ ይኾናል። ሰው ርህራሄ ሲያደርግ ዘመኑ የርህራሄ ይኾናል። ሰው ክፉ ካደረገ ግን ዘመኑም የክፋት ይኾናል ይላሉ። ዘመኑ ይቀደስ ዘንድ እርስ በእርስ ተወደዱ፤ ዘመን ይባረክ ግን በፍቅር ኑሩ።
እግዚአብሔር ይህችን ዓመት ቀድሷት እንዳለ ዓመቷን እንቀድሳት፤ ዓለም መገዳደሉን ይተው፤ ጨካኙ ጭካኔውን ይተው፤ ቀማኛውም መቀማቱን ትቶ ይመለስ፤ ክፉ የሚያደርግ ከክፋት ይመለስ፤ ደግነትን የሚያደርግም ደግነቱን ያስፋ ያ ሲኾን ዓመቷ ትቀደሳለች ብለዋል ሊቁ።
በቸርነት ተሰጥታለችና ይህችን ዓመት ቀድሷት፤ በቸርነት ታድላለችና ይህችን ዘመን አክብሯት፤ በትህትና ተሰጥታለችና ይህቸን ዓመት ትህትናን አድርጉባት፤ መልካሙን ገድል ተጋደሉባት፤ ከክፋት ራቁባት፤ ከጠብም ተጠበቁባት። ዘመንን ቀድሱ፤ ለመልካም ግብርም ተነሱ። አዲስ ዘመን ነውና።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!