በችግር ወቅት የደረሰ ግዙፉ የሲሚንቶ ፋብሪካ

2
ባሕር ዳር: መስከረም 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ግድቦች፣ ድልድዮች፣ ሕንጻዎች እና ሌሎችም የግንባታ ሥራዎች የተሳለጠ ግብዓት ሲኖራቸው ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጠራሉ፣ ሀገርም ትገነባለች። ከግንባታ ግብዓቶች መካከል ሲሚንቶ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል።
ባለፉት ዓመታት የሲሚንቶ ምርት በቀነሰ ቁጥር የዋጋው ነገርም እየናረ በግንባታው ዘርፍ ላይ አሉታዊ ጫና አሳድሮ መቆየቱ ይታወሳል። ዘርፉ በባህሪው ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ቢኾንም መጎዳቱ ደግሞ የወጣቶችን ኑሮ ጭምር ጎድቶ ነበር።
ይህ የሲሚንቶ ችግር ይፈታ ዘንድ” ሀገር እንገነባለን” የሚል ህልም ይዞ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ለሚ ከተማ አቅራቢያ የተጀመረው ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በ2017 በጀት ዓመት እውን ኾኖ ፍሬ መስጠት ጀምሯል። ዓመቱ የሲሚንቶ ገበያው የጠገበበት፣ ዋጋውም ቢኾን የተረጋጋበት እና የግንባታ ዘርፉም መነቃቃት የታየበት ነበር።
ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ጥሬ እቃን ከምቹ የኢንቨስትመንት አካባቢ ጋር አጣምሮ በያዘው እንሳሮ ወረዳ በ187 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። የግንባታው ወጭም 600 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ፈጅቷል ተብሏል። ይህንን ወጭ አሁን ባለው የምንዛሬ መጠን ሲታሰብ 84 ቢሊዮን ብር አካባቢ ማለት ነው።
ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሀገራዊ ፋይዳው የላቀ ነው። በቀን 150 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ የማምረት አቅም አለው። ይህ ማለት በሀገሪቱ ያሉ ሁሉም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ተደምረው ከሚያመርቱት ውስጥ ግማሹን ያህል ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ያመርተዋል ማለት ነው።
ከለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያም ግዙፍ አቅም አለው። ከ20 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል አስገኝቷል። ፋብሪካው የራሱን ትላልቅ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት በመላው ኢትዮጵያ ምርቶቹን እያደረሰም ይገኛል።
ይህ በአፍሪካ የገዘፈው ሀገራዊ ጥም ቆራጭ ፋብሪካ ግንባታው ተጠናቅቆ እውን የኾነው በ2017 ዓ.ም ስለነበር ዓመቱን በዘርፉ እመርታ የተመዘገበበት ያደርገዋል።
2018 ዓ.ምን በእንቁጣጣሽ ተቀብለናል። በአማራ ክልል የተጀማመሩ ሌሎችም ትላልቅ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አሉ። በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረንታ ወረዳ የሚገነባው በረንታ ሲሚንቶ ፋብሪካ እና በደጀን ወረዳ የሚገነባው ዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ የዓባይ ሸለቆን ተከትለው የሚገነቡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችም ልክ እንደለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በወቅቱ ተጠናቅቀው ተጨማሪ አቅም እንዲኾኑ፣ የሲሚንቶ ገበያውንም እንዲሞሉ ይጠበቃል።
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ እንዲህ አይነት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የሥራ እንቅስቃሴ እየተከታተለ፤ ጥንካሬ እና ውስንነቶቻቸውንም በቀጣይ ለተከታዮቹ የሚያደርስ ይኾናል።
መልካም አዲስ ዓመት!
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለአዲስ ዓመት ማዕድ አጋሩ።
Next article“ይህችን ዓመት ቀድሷት፤ ይህችን ዘመን አክብሯት”