
ባሕር ዳር፡ መስከረም 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ዘመን ስሌት መሠረት መስከረም አንድ ቀን ዓመተ ምህረት ይለወጣል። ዕለቱ የዘመን መለወጫ በመባልም ይታወቃል። ይህ በግእዝ ቋንቋ ‘ርዕሰ ዓውደ- ዓመት’ ይሰኛል።
የባሕር ሐሳብ ሊቃውንት ደግሞ መስከረም አንድን ለምን የዘመን መለወጫ እንደኾነ ሲያትቱ “ብርሃናት፦ ፀሐይ፣ ጨረቃ እና ከዋክብት የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜን ወር ጨርሰው መስከረም አንድ ስለሚጀምሩ ነው” በሚል አስፍረዋል።
ደራሲ ካሕሳይ ገብረ እግዚአብሔር የመስከረም ወርን “ቀዳማይ፣ ርዕሰ ክራሞት፣ መቅድመ አውርኅ፣ ርዕሰ ዐውደ-ዓመት፣ የክረምት ጫፍ መካተቻ፣ የመፀው መባቻ” ሲል ተንትኖታል።
የመስከረም ወር ለኢትዮጵያውያን የተስፋ ወር ነው፤ ፍኖተ ሰላምም ይሰኛል።
የዕንቁጣጣሽ አመጣጥን መልከ-ብዙ አተያዮች እንዳሉት የባሕረ ሃሳብ ሊቃውንት ይጠቀሳሉ።
በአንድ በኩል “ዕንቁ ዕፅ አመጣሽ” ብሎ የአበባ መፈንዳትን ለማመላከት እንደኾነ የሚጠቅሱ ወገኖች አሉ።
ንግሥት ሳባ ወደ ንጉሥ ሰሎሞን የእጅ መንሻ ይዛ ስትሄድ ንጉሡም “ዕንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንሽ” በሚል ቀን ከሌሊት የሚያበራ ቀለበት ስለሰጣት ነው የሚሉ ወገኖችም ይገኛሉ።
የስያሜው መነሻ ያም ኾነ ይህ መስከረም ለመልክዓ ምድሩ፣ ለሰው እና ለእንስሳት ሁሉ የሰላም፣ የፍስሐ እና የተድላ ወር ለመኾኑ ሁሉንም ያስማማል ነው የሚባለው። ለዚህም አይደል ሕጻናት፦
“መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ፣
እንኳን ሰው ወገኑን ይጠይቃል ባዳ”
የማለታቸው አንድምታም ሰው-ሰውን የመውደዱ ፍካሬ ነው።
አዋቂዎችም፦
“ክረምት አልፎ በጋ መስከረም ሲጠባ፣
አሮጌ ዓመት ሄዶ አዲሱ ሲገባ፣
በአዲስ ዓመት አዲስ ይታሰባል፣
ምኞት ይታቀዳል፤ ተስፋ ይታለማል፣
ሁሉም በየቤቱ እንደ አዲስ ይነቃል፣
ሁሉም በየሞያው በአጭር ይታጠቃል፡….”
የማለታቸው ምሥጢር በመስከረም እንደ አዲስ አቅደው በተስፋ የሚነሳሱበት የዓመት መጀመሪያ በመኾኑ ነው ይላል ገጣሚ ተፈሪ ዓለሙ።
በመስከረም ወር ምድር ዓደይ አበባ ትፈካለች። ውኃው ይጠራል። ሰማዩም የክብር ብርሃኑን ይገልጣል። ጥቁር ደመና ይገፈፋል፤ ክዋክብት እንደፈንዲሻ ይደምቃሉ። የዕጽዋት እና አዝዕርት እንቡጦች ይፈነዳሉ።
የመብረቅ ነጎድጓድ ተወግዶ የሰላም እና የሲሳይ ዝናብ ይርከፈከፋል።
እንስሳት ኩል የመሰለ ውኃ እየጠጡ ለምለም ሳር እየጋጡ ይቦርቃሉ።
በእርሻ ሲማስኑ የከረሙ በሬዎች እና በጭነት የከረሙ አጋሰሶች መስከረም ወር አንጻራዊ የእፎይታ ወራቸው ነው።
በክረምት አድፍጠው የከረሙ ንቦች አበባ ቀስመው ቀፏቸውን ይሞላሉ። ይወልዳሉ።
በ’ዕንቁጣጣሽ’ ምድር ብቻ አይደለችም የምትዋበው። መስከረም ለሰው ልጆችም በተለይም ለወጣቶች የፍቅር ወር ነው። ሰላም፣ ንጹህ አየር፣ የጤና ድባብ በየአካባቢው ያረባል።
“ክረምት አልፎ በጋ መስከረም ሲጠባ፣
አሮጌ ዓመት ሄዶ አዲሱ ሲገባ፣
አደይ ተከናንባ እንቁጣጣሽ ስትደምቅ፣
ምድር በልምላሜ በፀሐይ ስትሞቅ፣
ምኞት ይታቀዳል፣
ተስፋ ይታለማል፤”ሲል ከያኒ ተፈሪ ዓለሙ “መስከረም በሆነ” በሚል ርዕስ የከተበውን ሥነ ግጥም ያትታል።
የበቆሎ እሸት ጥብሱ፤ የቅቤ ልውሱ፤ የቅቤ በረካው አየሩን ያውደዋል። ለዚህም ነው፦
“…ይሸታል ጠጅ ጠጅ፣
የጌቶችም ደጅ “መባሉስ ለዚህም አይደል።
‘ሰኔ መጣና ነጣጠለን’ ብለው ወርሐ ሰኔን የረገሙ ተማሪዎች ተናፋቂያቸውን ያገኛሉ፤ ስለኾነም፦
“መስከረም ለምለም፣
አገናኜን አክርሞም..”
ሲሉ ያወድሱታል፤ ያሞካሹታል።
እንደ መውጫ
የዕንቁጣጣሽ ዕለት! በአዲሱ ዓመት! 2018 ዓ.ም ብረት የያዙ ሁሉ ልባቸውን ለሰላማዊ ክፍት የሚያደርጉበት ይሁን!
አዎ! በዕንቁጣጣሽ ዕለት በ2018 ዓ.ም ሁላችንም ኢትዮጵያ ሰላም ውላ ሰላም ታድር ዘንድ ከምርቃት ባሻገር ለሰላም ልንተጋ ይገባናል።
መልካም አዲስ ዓመት!

ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን