ብስራት ነጋሪዋ አደይ አበባ

2
ባሕር ዳር፡ መስከረም 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እንቁጣጣሽ ወይም የዘመን መለወጫ፣ ለአዲስ ሕይወት፣ ለመልካም ሥራ፣ ለስኬት እና ለአብሮነት የምናቅድበት ልዩ ቀን ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ባሕር ዳር ከተማ የጽርሃ ጽዮን ቤተክርስቲያን ስብከተ ወንጌል መምህር ይትባረክ ደምለው የዘመን አቆጣጠር ከመስከረም ወር የሚጀምረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም ስላለው ነው ይላሉ።
መሥከረም የኢትዮጵያ ወራት መጀመሪያ ሲኾን የመጀመሪያው ቀን ደግሞ ዘመን መለወጫ፣ እንቁጣጣሽ ወይም ቅዱስ ዮሐንስ ተብሎ ይጠራል ብለዋል።
👉የዘመን መለወጫ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ አመጣጥ
መምህር ይትባረክ የዘመን መለወጫ መጀመርያ ታሪክን በተመለከተ ሦስት ጉዳዮችን ያነሳሉ። አንደኛው በኖህ ዘመን የጥፋት ውኃ ማቆሙን ለማወቅ የተላከችው ርግብ ለምለም ቄጠማ እና አደይ አበባ ይዛ ተመለሰች፤ ይህ የፍዳ እና የኩነኔ ዘመን ማለፉን እና የድኅነት ዘመን መምጣቱን ያሳያል ነው ያሉት። በዚህም ምክንያት አዲሱ ዓመት ዘመን መለወጫ ተብሎ መጠራት ጀመረ ሲሉም ያብራራሉ።
ሁለተኛው ኖህ ለሦስቱ ልጆቹ አሕጉራትን ሲያካፍል፣ አፍሪካ ለካም ደረሰች፤ ካም ወደ አፍሪካ ሲገባ መጀመሪያ ያረፈው በኢትዮጵያ ሲኾን ያኔም ሀገሪቱ በአደይ አበባ አሸብርቃ ነበር፤ ይህን ውበት ሲያይ በመደሰቱ ወቅቱን እንቁጣጣሽ ብሎ ጠርቶታል ሲሉም ያስረዳሉ መምህሩ።
ሦስተኛው ጉዳይ ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ የንጉሥ ሰሎሞንን ጥበብ ለማየት ስትሄድ ንጉሡም በደስታ ተቀበላት፤ የመጣችበት ወር መስከረም በመኾኑም የአደይ አበባ ቅርጽ ያለው “እንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንሽ” በማለት በቀን እና በሌሊት የሚያበራ ቀለበት እንደሰጣት ይገልጻሉ። ይህም የደስታ እና የመዋደድ ብስራት ተብሎ ይታሰባል ብለዋል።
👉የአደይ አበባ እና እንቁጣጣሽ ትስስር
የዘመን መለወጫ እና አደይ አበባ የተሳሰሩበት ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ተፈጥሮሯዊ ምክንያቶች አሉ የሚሉት መምህሩ አደይ አበባ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለስምንት ቅጠል ስትኾን “ድርብ መስቀል” ትባላለች ነው ያሉት። የቅጠሎቿ ቁጥርም ሃይማኖታዊ ትርጉም እንዳለው ነግረውናል።
በተፈጥሮዋ አደይ አበባ ከጥር ወር በኋላ ትጠፋ እና ፍሬዋ መሬት ውስጥ ይገባል፤ በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ እንደገና በቅላ በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ደግሞ ውበቷን ትገልጣለች። ይህም የክረምት ወቅት ማለፉን፣ ደመናው ጠርቶ መስኩ አረንጓዴ መልበሱን እና አዲስ የፍሬ ዘመን መጀመሩን ያመለክታል ሲሉም መምህሩ አብራርተዋል።
በዚህም ምክንያት አደይ አበባ የዘመን መለወጫን የምታበስር አበባ በመኾን የራሷን ትርጉም አግኝታለች ነው ያሉት።
አደይ አበባ ሁሉም ሰው በጉጉት የሚጠብቃት የብስራት ምልክት ኾና ዘመናትን ስለመሻገሯም መምህሩ አስረድተውናል።
መልካም አዲስ ዓመት!🌻
ዘጋቢ፦ ሰማሀል ፍስሀ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article“ከቆመው ድልድይ ስር የማይቆም ወንዝ አለ”
Next articleዕንቁጣጣሽ-የሰላም ፍኖት