“ከቆመው ድልድይ ስር የማይቆም ወንዝ አለ”

2
ባሕር ዳር: መስከረም 1/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወንድሞቹን በበደለ እና ሀገርን ባጎሳቆለ መንፈስ አዲስ ዓመትን መቀበል ትክክል አይኾንም፡፡ ትዕቢትን ባስተናገደ አንደበት፣ ቁጣን በተናገረ ምላስ እና ጥላቻን በዘራ አዕምሮ ዘመንን መቀመር፤ ዓመትን መቀየር “ወይኑን እንደማይመጥን አቁማዳ” ነው፡፡
አዲስ ዘመን ተስፋ ነው፡፡ የተስፋው ባለቤቶች ደግሞ የሰው ልጆች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ አዲስ ዘመን በወርሃ መስከረም ይጠባል፡፡ “ሰው ዘመንን ይቀይራል ወይስ ሰው በዘመን ይቀየራል” ብሎ ማሰብ ግን ግድ ይላል፡፡
ጸሐፊው እንዳለው መስከረም ጠባ፡፡ የመስከረም ጮራ እንቁጣጣሽ ብላ ቱግ አለች፡፡ ልጃገረዶች ሳዱላቸውን አሳመሩ፤ አደስ ተቀቡ፤ እንሶስላ ሞቁ፤ ወንዝ ወረዱ፤ ቄጠማ ለቀሙ፡፡ ጸአዳ ልብሳቸውን ለብሰው፣ አሸንክታባቸውን አጥልቀው፣ “አበባየ ሆይ – ለምለም…” በማለት ተሠባሥበው ብቅ አሉ፤ ልክ እንደ ጮራይቱ፡፡
የወርሃ መስከረም ብሩህ ተስፋ እና ስሜት በምድሪቱ አስተጋባ፡፡ ጠፈፍ እያለ መጣ ምድሩ፡፡ ወንዙም እየጠራ፡፡ ኩል መሰለ ሰማዩ፡፡ ሜዳው፣ ጋራ፣ ሸንተረሩ ወርቃማ የአደይ አበባ ካባ ለበሰ፡፡ ደመራ ተደመረ፡፡ ተቀጣጠለ ችቦ፡፡ ‘እዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባየ’ ተባለ፤ የወራት ንጉሥ የአዲስ ዓመት ልብስ የኾነው መስከረም ሲጠባ፡፡
መስከረም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ልዩ ነው፡፡ የክረምቱ ጨለማ ማብቃት ተብሲር፤ የአዲስ ብርሃን እና ዘመን መምጣት ብስራት ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ “እዮሐ የበርበሬ ውኃ፤ በሽዋ በጎንደር፤ በትግሬ፣ በሐረር… ያላችሁ እንዴት ከረማችሁ” እየተባለ ዘመድ ከዘመድ፤ ወላጅ ከወዳጅ ይጠያየቃል፡፡
ጭፍናው የክረምት ወራት አልፎ ደመና እና ጉሙ የተገፈፈለት ሰማይ፣ የጠራ ጅረት እና የረጋ ምድር ከመስከረም ይጀምራል፡፡ ፀሐይ፣ ጨረቃ እና ከዋክብት የዓመቱን ሥራቸውን አጠናቅቀው በአዲስ እንደ አዲስ ይጀምራሉ፡፡ ዘመን ከማቴዎስ ወደ ማርቆስ፤ ከማርቆስ ወደ ሉቃስ፤ ከሉቃስ ወደ ዮሐንስ እና ከዮሐንስ ወደ ማቴዎስ በየተራ ይፈራረቃሉ፡፡
መስከረም የዘመን መፈራረቅን ብቻ ሳይኾን የአስተሳስብ ሽግግርም ይደረግበታል፡፡ እረኛ ለከብቱ፣ ተማሪ ለትምህርቱ፣ ገበሬ ለምርቱ፣ ዳኛ ለችሎቱ በአዲስ ይዘጋጃሉ፡፡ በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ፣ አዲስ ሕይዎት እና አዲስ ዕቅድ በየሁሉም ጎጆ ይቀለሳል፡፡ አሮጌውን ጥሎ አዲሱን አንጠልጥሎ ከትናንቱ አንድ እየተጨመረ ሕይዎትን ወደፊት በተስፋ ያማትራሉ፡፡ በመስከረም እምቡጥ የኾነው ይፈነዳል፤ ጮርቃው መብሰል ይጀምራል፡፡
የአዳምን መምጣት ተከትሎ በሚሰላው ዓመተ ዓለም ሲቆጠር ዓለም ከተፈጠረ 7 ሺህ 518ኛውን እና ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባለው አቆጣጠር ደግሞ 2 ሺህ 18ኛውን አዲስ ዓመት ኢትዮጵያውያን ዛሬ ተቀበሉ፡፡ የዘመን መፈራረቅ ዑደታዊ መስተጋብር ነው፡፡ ዘመን ጊዜውን ጠብቆ ወራቱን አውቆ ከልዩ ልዩ ክስተቶች ጋር ሳያሰልስ መጥቶ ያልፋል፡፡ ተፈጥሯዊ ሕግ ስለኾነ ባለበት አይቆምም፡፡
ዛሬ ለነገ ትናንትነቱ፤ ዘንድሮ ለከርሞ አምናነቱ ተፈጥሯዊ ዑደት ነው፡፡ “ከቆመው ድልድይ ስር የማይቆም ወንዝ አለ” እንዲሉ ድልድይ የኾነው የሰው ልጅ ወንዝ የኾነውን ዘመንን ሳያቆራርጥ ያሳልፋል፡፡ የአገልግሎት ዘመኑ የበዛ እና ያረጀ ድልድይ ተደርምሶ አደጋ እንዳይኾን ፈርሶ እንደሚታደስ ሁሉ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ሕግ ራሱን ተክቶ በዘመን ያልፋል፤ ምድሪቱንም ለሚቀጥለው ያወርሳል፡፡ ዘመን ቅብብሎሽ ነውና፡፡
በዘመን መለወጫ ላይ የሰው ልጅም ሕይዎት ሊለወጥ ይገባል፡፡ ጮርቃ አስተሳሰብ ሊበስልም ግድ ይላል፡፡ በመረጃ ዘመን ላይ ቆሞ በድንጋይ ዘመን እሳቤ አዲስ ዓመት መቀበል እንዴት ይቻላል? ወንድም ወንድሙን እያጠቃ፤ መነጋገር እና መግባባት እየተቻለ በጦርነት እና በግጭት ልዩነትን ለመፍታት እየተሞከረ አዲስ ዓመትን መቀበል እንዴት ሊኾን ይችላል? ከዘመን ቀድሞ የሰው ልጅ በአስተሳሰብ ሊለወጥ ግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም የዘመን ጌታው የሰው ልጅ ነውና፡፡
ወንድሞቹን በበደለ እና ሀገርን ባጎሳቆለ መንፈስ አዲስ ዓመትን መቀበል ይከብዳል፡፡ ትዕቢትን ባስተናገደ አንደበት፣ ቁጣን በተናገረ ምላስ እና ጥላቻን በዘራ አዕምሮ ዘመንን መቀመር፤ ዓመትን መቀየር “ወይኑን እንደማይመጥን አቁማዳ” ነው፡፡
አዲስ ዓመትን ስንቀበል ዘመን ብቻ ሳይኾን አስተሳሰብ ሊቀየር ግድ ይላል፡፡ አደይ አበቦች ብቻ ሳይኾኑ የአስተሳሰብ ርዕዮት ሊፈነዳ ያስፈልጋል፡፡ አዝርዕት ብቻ ሳይኾን አስተሳሰብ መብሰል ይኖርበታል፡፡ ከዘመን ዘመን መሸጋገር ቀመሩ እና ቁጥሩ እንደተጠበቀ ኾኖ አዲስ እሳቤ፣ አዲስ ዕይታ፣ አዲስ መነሳሳት እና አዲስ ፍላጎት ያስፈልጋል፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ እንሰንቅ”
Next articleብስራት ነጋሪዋ አደይ አበባ