
ባሕር ዳር፡ መስከረም 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ቀድሞ የቆየንበት ዓመት አሮጌ ተብሎ ቀጣዩ ዓመት አዲስ የሚል ስያሜ ይሰጠዋል።
ይህ የዘመን ብያኔ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለመደ እና ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነው።
አዲሱን ዓመትም በደስታ፣ በተስፋ፣ በስኬት እና በጥሩ መንፈስ ለመዝለቅ የዘመን መለወጫ በዓልን በድምቀት በማክበር ነው ዓመቱ የሚጀመረው።
አብዛኛው ሰው በአዲስ ዓመት በሕይዎቱ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ይመኛል፣ ከአዲሱ ዓመት ጋርም አብሮ መለወጥ ይፈልጋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የጽርሐ ጽዮን መንፈሳዊ ኮሌጅ ዲን መጋቢ ምስጢር ስማቸው ንጋቱ በዘመን ዑደት ዓመታት ይቀያየራሉ ይላሉ።
ዓመት አልፎ ሌላ ዓመት ሲተካ የዘመን እና የወቅቶች ዑደትም እንዲሁ ይኾናል ሲሉ ያብራራሉ።
የዘመን ቁጥር እየጨመረ፣ ወቅቶች እየተቀያየሩ፣ በዚያው ልክ የሚኖሩት ሁለንተናዊ ለውጦችን መሠረት በማድረግ አዲስ ዓመት እያልን እንጠራዋለን ብለዋል።
ሰው አዲሱን ዓመት ሲቀበል ተስፋ የሚያደርገው ነገር መኖር ያስፈልገዋል ይላሉ።
በተለይም ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እንደ 13 ወር ጸጋ የኾነችውን የጳጉሜን ወር ደግሞ ለአዲሱ ዓመት የምንዘጋጅበት፣ ቆም ብለን የምናሰላስልበት፣ እና ለአዲሱ ዓመት የምናቅድበት ወርቃማ ወቅት እንደኾነችም ነው ያነሱት።
“የባለፈውን ዓመት ሁኔታ መለስ ብለን በመቃኘት እና በመገምገም ራሳችንን የምናይበት እና የምንታዘብበት ወቅት ነው” ብለዋል።
ከዚህ በመነሳትም ለቀጣዩ አዲስ ዓመት ሕይዎት፣ ተግባር መሠረት የምንጥልበት እና የምናቅድበት መኾኑንም ያብራራሉ።
አዲስ ዓመት ሲመጣ ሁሉም በያለበት ተስፋ ይሰንቃል፣ ተስፋ የሚሰንቀውም ያሳለፈውን ጊዜ አስቦ ነገን በተሻለ ለመኖር በማሰብ እንደኾነ ነው የሚገልጹት።
በአዲስ ዓመት በጎ ነገርን አስቦ በአዕምሮ ማስቀመጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት። በዚህ መንገድ አቅደን ተስፋ አድርገን አዲሱን ዓመት ከተቀበልነው በስህተት እንኳን መጥፎ ሥራ ብንሠራ አዕምሯችን ይከሰናል ነው ያሉት።
ሰው የሚኖረው ተስፋ ያደረገውን እና ቀድሞ አዕምሮው ውስጥ ያስቀመጠውን እሳቤ ነው ይላሉ።
ለስኬትም ለውድቀትም ተስፋ የምናደርገው እና በአዕምሯችን የምናስቀምጠው የተስፋ ስንቅ ወሳኝ ነው ብለዋል።
አዕምሮን በአዲስ ተስፋ እና በአዲስ አስተሳሰብ በመቅረጽ ብሎም በመዘጋጀት አዲሱን ዓመት መቀበል እንደሚያስፈልግም መክረዋል።
ይህም ዓመቱን መሉ ለምናከናውነው ስኬት ስንቅ የሚኾን እንደኾነም ነው ያስረዱት።
“ቸር ተመኝ፤ ቸር እንድታገኝ” እንዲሉ በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ ሰንቆ ለስኬት የሚያበቃውን አዎንታዊ አስተሳሰብ መያዝ ያስፈልጋል።
አዎንታዊ አስተሳሰብ በስኬት እንዲገለጽ ከምኞት በዘለለ ሁሉም በየተሰማራበት የሥራ ድርሻም ኾነ በግል ሕይዎት ዓመቱን ሙሉ በዕቅድ ማከናወን እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን