“ታላቁን የሕዳሴ ግድባችንን ስናይ ለልማት እንበረታለን” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

4
ባሕር ዳር፡ ጳጉሜን 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በኅብር ወደ ክብር ብለዋል።
ንጋት እና ብርሃን ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድባችን እንደ ወንዛችን ዓባይ ባለግርማ፣ እንደ ተፋሰሱ እየተደመሩ ኃያል የመሆን፣ እንደግስጋሴው የጽናት አብነት ነው።
ከጉባ ተራራ ስር ጀምሮ የተዘረጋ ራዕይ፣ ጽናት፣ ኅብረት፣ ትዕግስትና ትጋት የተጻፈበት የውኃ መጽሐፍ ነው ያሉት።
የሕዳሴ ግድባችን በትውልዶች ልብ እና ህሊና የነበረ፣ በብርቱዎች ዘመን የተፈጸመ፣ ባለ ርዕዮች በኅብርና በጀግንነት የተሰለፉለት የድል ሰንደቅ ነው ብለውታል።
ታላቁ ግድባችን ስለኢትዮጵያውያን ብሎም አፍሪካውያን ታላቅነት ነጋሪ ከሆኑት መካከል ነው።
ሁላችንም እንደ ሕዝብ፣ ለመንግሥትም እንደ አገልጋይ በአንድ ልብ ወደአለምነው የጋራ ግብ ለማንሰራራት፣ የእስከዛሬ ጥረት እና ውጤቶቻችንን ለማጽናት ምልክት እና ምስክር የሆነ፣ በሰፊ አድማስ ያበራነው የአፍሪካ ብርሃን እና ከፍ አድርገን ያቆምነው የቀጣናው የልማት ምሰሶ ነው።
ታላቁን የሕዳሴ ግድባችንን ስናይ ለልማት እንበረታለን። ለማንሰራራት እንተጋለን። ለሰላም እና ለሀገራዊ ኅብረት በጋራ እንተማለን። ውኃችን ብርታታችን ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ሕንጻ ከመሠረት፤ ትውልድ ከልጅነት መታነጽ አለባቸው” የእድገት ሳይኮሎጅ ምሁር
Next articleበአገው ግምጃ ቤት ከተማ አሥተዳደር የተለያዩ መሠረተ ልማቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።