“ሕንጻ ከመሠረት፤ ትውልድ ከልጅነት መታነጽ አለባቸው” የእድገት ሳይኮሎጅ ምሁር

7
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እነኾ አሮጌው ዓመት አልቆ የአዲስ ዓመት ላይ ደርሰናል። የዛሬ ጳጉሜን 05/2017 ዓ.ም ወደ ነገው 2018 ዓ.ም መሸጋገሪያ ድልድይ ነው። ጳጉሜ 5 “የነገው ቀን” ተብሎም ታስቦ ይውላል።
ሰው ሁሉ የተሻለ ነገን ይናፍቃል። አሮጌ ዓመት ሄዶ አዲስ ዓመት በገባ ቁጥር ሁሉም ሰው ያለፈው ክፉ ነገር ሁሉ ዳግም በሕይወቱ እንዳይመጣ ይሻል። መልካም ነገርን ይመኛል፤ ቸር ነገርን ይናፍቃል፤ የሀሳብ መሟላት እና ሁለንተናዊ እድገትን ይናፍቃል።
ያማረ እና የሰመረ ነገ የሚሠራው ዛሬ ነው። ዛሬ ላይ ቆሞ ነገን አሻግሮ በማየት፣ ልጅነት ላይ ቆሞ ወጣትነት እና እርጅናም እንዳሉ ባለመዘንጋት፣ የዛሬ ብርቱ ሥራ ለነገ ምቹ ሀገር ዋስትና እንደኾነም አውቆ እና ተልሞ በመሥራት ዛሬውኑ ነገን ማስተካከል ይቻላል።
ነገን የማያ ደግሞ አንድ ሁነኛ መነጽር አለ፤ እሱም ትምህርት ነው። ትምህርት ሰዎች አዲስ ነገሮችን የሚያውቁበት፣ በተለይም ልጆች አካባቢያቸውን የሚለዩበት፣ የነገ የጎልማሳነት ሕይወታቸውን ዛሬ ላይ የሚያንጹበት መሳሪያ ነው ይላሉ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የእድገት ሳይኮሎጅ መምህርና ተመራማሪው ውሀቤ ብርሃን(ዶ.ር)።
የዕይታ አድማስን የሚያሰፉበት፣ ዓለምን የሚገናዝቡበት እና ነገን በወጉ የሚተልሙበት፣ የተሻለ ሀገር ሠርተው ለትውልድም የሚያሸጋግሩበት ነው ሲሉም ያብራራሉ።
ከትምህርት እና ከዕውቀት መነጠል ደግሞ ከዛሬ ያልተሻለ ወይም የባሰ ነገን ለመቀበል ራስን ማመቻቸት፣ ምሉዕነት የጎደለው ኑሮ ለገፉት እና ችግሮች ያጠሉበትንም ሀገር ለመጭው ትውልድ ለማሻገር እንደመፍቀድ ያለ ስለመኾኑ ከምሁሩ ንግግር መገንዘብ ይቻላል።
ስለትምህርት በተጨባጭ የገጠመንን ነገር ስናይ በአማራ ክልል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በርካታ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ እርቀዋል። ይህም ልጆች በዕድሜያቸው መማር ያለባቸውን ትምህርት እንዳይማሩ እንቅፋት ኾኖ ቆይቷል።
መምህርና ተመራማሪው ውሀቤ ብርሃን(ዶ.ር) ትምህርት ለልጆች እንደምግብ ነው ይላሉ። ለአካላዊ እድገታቸው ምግብ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ለነገ ሕይወታቸው መሠረት ለኾነው አዕምሯዊ እድገታቸው ደግሞ ትምህርት አስፈላጊ ነው ብለዋል። አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ እይታቸው እንዲጎለብት ትምህርት ቤት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
“ሕንጻ ከመሠረት፤ የነገ ተወዳዳሪ ትውልድም ከልጅነት መታነጽ አባቸው” ይላሉ ምሁሩ። ከመሠረቱ ያላነጽነው ግንባታ እያደገ የሚሄደውን ፎቅ ለመሸከም እንደማይቻለው ሁሉ፤ ከልጅነታቸው ያላስተማርናቸው ሕጻናትም በቀጣይ የትምህርት ሕይወታቸው ተወዳዳሪ አይኾኑም በማለትም አብራርተዋል። በመኾኑም ልጆች እንደየ ዕድሜ ክልላቸው ማግኘት ያለባቸውን ዕውቀት እና የትምህርት ደረጃ እያገኙ ማለፍ እንዳለባቸው መክረዋል።
ልጆች ትምህርት ቤት ሲገኙ የተቀረጸውን የክፍል ትምህርት ከመማር ሌላ ከጓደኞቻቸው ጋር እና እርስ በእርሳቸው ይማማራሉ፣ አንዱ ከሌላው እየተወዳደሩ ራሳቸውን ያውቃሉ ነው ያሉት።
“የልጅነት ጊዜ እንደ ችግኝ ነው” ያሉት ምሁሩ ችግኝ በችግኝነቱ በአግባቡ እንክብካቤ ካላገኘ አድጎ ዛፍ ሊኾን እንደማይችል ሁሉ በልጅነታቸው ያልተማሩ እና በሥነ ምግባር ያልታነጹ ልጆችም የነገ ሀገራዊ ኅላፊነታቸውን ለመሸከም እንደሚቸገሩ አብራርተዋል። በሁሉም ነገር የበቃ እና ተረካቢ የሌላት ሀገር ደግሞ ከዓለም ጋርም የመወዳደሩ ነገር ያዳግታታል።
ልጆች በየዕድሜ ክልላቸው የተከፋፈለ ማወቅ የሚገባቸው የትምህርት አይነት አለ፤ በመኾኑም ያለማቋረጥ በትምህርት ቤት መገኘት አለባቸው ብለዋል ተመራማሪው።
የነገዋን ሀገር ተረክበው የሚያስቀጥሉት የዛሬ ልጆች ናቸው፤ እነዚህን ልጆች ብቁ አድርጎ መገንባት ደግሞ ለነገ ዋስትና ነው ብለዋል። ወላጆች ለልጆቻቸው ትምህርት ሲሉ ይትጉ፣ መምህራን በችግር ውስጥ ያለውን የልጆች ትምህርት ለማቃናት የተለመደውን ጥረታቸውን ያጠናክሩ፣ ነገ የተሻለ ሀገር እንዲኖረው የሚፈልግ አካል በሙሉ ለትምህርት እና ትምህርት ቤቶች ጠበቃ ይሁን ሲሉም መክረዋል ዶክተር ውሐቤ።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበ2018 የትምህርት ዘመን 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመገብ ማቀዱን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
Next article“ታላቁን የሕዳሴ ግድባችንን ስናይ ለልማት እንበረታለን” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ