በ2018 የትምህርት ዘመን 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመገብ ማቀዱን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

4
ባሕር ዳር፡ ጳጉሜን 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ትምህርት ንቃትን ይጠይቃል፤ ሕጻናት ንቁ ኾነው እንዲማሩ ደግሞ የተሟላ ሥርዓተ ምግብ ማግኘት ይኖርባቸውል። የተማሪዎች ምገባ ለውጤታማ የትምህርት አቀባበል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ይህንን መነሻ በማድረግ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር ቀደም ብሎ መጀመሩ ይታወሳል።
በአማራ ክልል በከተማ አሥተዳደሮች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ለመመገብ ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኀበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ባለፈው ዓመት በችግር ላይም ኾነን ከ294 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ስንመግብ ቆይተናል ብለዋል።
የምገባ መርሐ ግብሩም ከመንግሥት፣ ከማኀበረሰቡ እና ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች በተገኘ ገቢ መካሄዱን ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመትም ለ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተማሪዎች ምገባ ለማካሄድ መታቀዱን ገልጸዋል። ለዚህ የሚኾነው በጀትም በመንግሥት፣ በአጋር አካላትና ከማኀበረሰቡ ለመሰብሰብ ታቅዷል ነው ያሉት።
የምገባ መርሐ ግብሩን ውጤታማ ለማድረግ ለባለ ድርሻ አካላት ተግባራትን ከፋፋሎ በመስጠት ሃብት የማሠባሠብ ሥራ እንደሚሠራም ነው የተገለጸው።
በዚህ መሠረትም ከ400 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በትምህርት ቢሮው አማካኝነት ለመመገብ እንደታቀደ ተናግረዋል። ቀሪው ድግሞ ማኀበረሰቡ እንደየ አቅሙ በማዋጣት፣ ድጋፍ በማድረግ እና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ትብብር የሚከናወን መኾኑን አንስተዋል።
በምገባ መርሐ ግብሩ በዋናነት ቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት። ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ኹሉንም አይነት አማራጮች ተጠቅመን የምገባ መርሐ ግብሩን በመፈጸም ለነገ ተተኪ ተማሪዎች መሠረት መጣል ያስፈልጋል ብለዋል።
ትምህርት ቤቶችም የወተት ላሞችን ገዝተው ለምገባ የሚኾን ወተት እንዲያቀርቡ ይደረጋል ነው ያሉት። ባለፈው ዓመት በአምስት ትምህርት ቤቶች ተሞክሮ ውጤት ተገኝቶበታል ብለዋል።
በተጨማሪም አትክልትና ፍራፍሬ እንዲያለሙ በማድረግ የተመጣጠነ ምግብ ለተማሪዎች ምገባ ለማዋል እየተሠራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ተማሪዎች በችግር ምክንያት ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል።
ከ1ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ደብተር መሰብሰቡንም ጠቁመዋል። በቀጣይ ቀሪ ጊዜያትም የማሠባሠቡ ተግባር የሚቀጥል ይኾናል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ኾነዋል፡፡
Next article“ሕንጻ ከመሠረት፤ ትውልድ ከልጅነት መታነጽ አለባቸው” የእድገት ሳይኮሎጅ ምሁር