በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ኾነዋል፡፡

5

ባሕር ዳር፡ ጳጉሜን 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቋል፡፡

 

የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አወቀ ዘመነ በበጀት ዓመቱ በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት 80 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ሢሠራ መቆየቱን ተናግረዋል።

 

ቢሮው በ2017 በጀት ዓመት በአጠቃላይ 1ሚሊዮን 233 ሺህ 744 ዜጎችን በጊዜያዊነት እና በቋሚነት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ መሥራቱን ያስታወሱት ምክትል ኀላፊው ለ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

 

በበጀት ዓመቱ ከ80ሺህ በላይ የሚደርሱ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እንደተፈጠረላቸውም አስታውቀዋል።

 

በበጀት ዓመቱ የሥራ ዕድልን ለመፍጠር ትልቅ አቅም የነበረው ከባለፉት ዓመታት በተለየ ሁኔታ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶችን አቅም አሟጦ መጠቀም መቻሉ ነው ብለዋል።

 

መንግስሥታዊ ካልኾኑ ተቋማት ብቻ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ ብድር በማሰራጨት የዜጎችን የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡

 

በዚህም ወደ 15 ሺህ ለሚደርሱ ኢንተርፕራይዞች እና 25ሺህ ለሚኾኑ አንቀሳቃሽ ግለሰቦች የብድር ተጠቃሚ እንዲኾኑ ተደርጓል ብለዋል።

 

በመደበኛ ብድር ደግሞ ከ4 ቢሊዮን 506 ሚሊዮን ብር በላይ በመስጠት ዜጎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ከፍተኛ ስርጭት እንደተደረገም ጠቁመዋል፡፡ይህ ገንዘብ ከባለፉት ዓመታት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር ትልቅ ብልጫ እንዳለውም ነው የተናገሩት፡፡

 

ዓመቱ ከ16 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የመሬት አቅርቦት በማድረግ 2ሺህ 52 የሚደርሱ ሸዶች በአዲስ ተገንብተው ለዜጎች እንዲተላለፉ መደረጉንም ገልጸዋል።

 

በሕገ ወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ 2ሺህ 500 ሸዶች እና 3ሺህ 700 ኮንቴነሮች እንዲመለሱ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ሃብት ለማፍራት የተደረገው ጥረት ከፍተኛ እንደነበርም አብራርተዋል፡፡

 

በቀጣይ በአምስት ዓመቱ ስትራቴጅክ ዕቅድ በክልሉ ከ5 ሚሊዮን 480 ሺህ በላይ ዜጎችን በጊዜያዊ እና በቋሚነት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል።

 

ከዚህ ውስጥ 80 በመቶ የሚኾኑት የቋሚ የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በ2018 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እቅድ መያዙንም ገልጸዋል።

 

100 ሺህ የሚኾኑት ዜጎች ደግሞ ለውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት የሚፈጠርላቸው ናቸው ተብሏል።

 

ይህም ዲጅታላይዝድ በኾነ እና ጥራቱን በጠበቀ አሠራር ተግባራዊ እንደሚኾን ነው የተናገሩት።

 

የተያዘውን ዕቅድ በተሳካ ሁኔታ ለመፈጸም የብድር ሰጭ ተቋማት እና የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የሚታይ፣ የሚጨበጥ እና እውነታነት ያለው ሥራ ለመሥራት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

 

ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ነገዋን እየሠራች ነው!” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት 
Next articleበ2018 የትምህርት ዘመን 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመገብ ማቀዱን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።