
ጎንደር: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጳጉሜን 04 የማንሠራራት ቀን በማስመልከት በጎንደር ከተማ አሥተዳደር እየተሠሩ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች አና የከተማዋ ነዋሪዎች እንዲኹም የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጎብኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኛው ጎንደር ከነበረችበት እና ከተገታው እድገቷ በልጆቿ ትብብር ወደ ቀድሞ ክብሯ እየተመለሠች መኾኗን ተናግረዋል። ጎንደር ከከተሜነት ታሪኳ ጋር አብሮ የማይሄድ ጉስቁልናዋ አብቅቶ የሕዳሴዋ ዘመን ላይ ስለመኾኗም አብራርተዋል።
የዛሬው ቀን አባይ የተገደበበት ቀን በመኾኑ ጭምር ልዩ ያርገዋል ያሉት አቶ ቻላቸው ይህ የማንሠራራት ዘመን እንዲቀጥል ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም ጉልበት እንዲኾንም ጠይቀዋል።
በጉብኝቱ የተገኙት መልዓከ ገነት ቄስ ፈንታ ገብረ ሚካኤል የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ውበት ያስጠበቀ እና ለሥራ ፈላጊዎችም የሥራ ዕድል የፈጠረ በመኾኑ ደስተኛ መኾናቸውን ነው የገለጹት።
ሌላው በጉብኝቱ የተገኙት የሀገር ሸማግሌ አስረስ መሐመድ ከዚህ በፊት የቆሻሻ መጣያ የነበረ ቦታ በዚህ መልኩ ውብ ኾኖ በማየታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። ልማቱ መቀጠል አንዳለበትም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ማርታ አዱኛ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!