“የሕዳሴ ግድቡ የታሪካችን እጥፋት እና ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚወስድ ፕሮጀክት ነው” የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት

8

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 4/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዳሴ ግድቡ የታሪካችን እጥፋት እና ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚወስድ ፕሮጀክት መኾኑን የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።

 

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡

 

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ ‘ኢትዮጵያውያን በተከታታይ ትውልዶች ሲዘከር የሚኖር ትልቅ አሻራ በማኖራችሁ እንኳን ደስ አላችሁ” ብሏል።

 

የሕዳሴ ግድቡ የታሪካችን እጥፋት እና ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚወስድ ፕሮጀክት መኾኑን አመልክቷል፡፡

 

ከመቆጨት እና ከቁዘማ በመውጣት በአፍሪካ አንደኛ የኾነ ግድብ በራሳችን አቅም መሥራት መቻል ትልቅ የሥነ-ልቦና ከፍታን እንደሚያስገኝ፤ በተጨባጭ የሚታይ የእይታ እና የከፍታ ለውጥ እንደሚያመጣም አስታውቋል፡፡

 

ሀገራችን በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ እንዳትሰራ እና እንዳታለማ ድጋፍ እና ብድር እንዳታገኝ ሲደረግ ነበር፡፡በራሳችን ገንዘብና በሕዝብ ጉልበት ግድቡን መሥራት መቻል ትልቅ ድል ነው ብሏል፡፡

 

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ቁልፍ መሠረት ልማቶችን በመጠበቅ ረገድ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን በግድቡ ግንባታ ሂደት በመረጃ ልቆ በመገኘት፣ አስቀድሞ አደጋን በማነፍነፍ እና ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ ታግዞ በማከናወን፤ ከግድቡ ጋር በተያያዘ የተከፈተውን የሥነ-ልቦና ጦርነት እና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች በመመከት እንዲሁም መላው ሰራተኛም በቦንድ ግዢ ከፍተኛ ሚና አበርክቷል ያለው መረጃው፤ የተቋሙ አባላት እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ በመክፈል ግድቡ ለፍጻሜ እንዲበቃ በማድረጋቸው ምስጋና እንደሚገባቸው አስታውቋል፡፡

 

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም በተለያየ ደረጃ የሚገለጽ አስተዋጽዖ በማበርከት ግድቡ እንዲጠናቀቅ ያደረገው ርብብር በታሪክ ሲወሳ የሚኖር ነው ብሏል፡፡

 

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ.ር) ግድቡ ከፍጻሜ እንዲደርስ በሳልና ቁርጠኛ አመራር በመስጠት ያበረከቱት ሚና ለሀገራችን የማንሠራራት ጉዞ አዲስ ምዕራፍ መሆኑን አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለኢዜአ የላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article” የሕዳሴ ግድብ አበርክቶ ለሌሎች ሀገራትም የሚተርፍ ነው” የውጭ ሀገራት የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኞች
Next articleታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዘመኑ ትውልድ የጋራ እና የወል እውነት መኾኑን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ተናገሩ።