
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚኖረው አበርክቶ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለሌሎችም ሀገራት እንደሚተርፍ ዩጋንዳውያን እና ኬንያውያን የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኞች ተናግረዋል።
ሞሰስ ክሪስፐስ ኦኬሎ ይባላሉ። እኝህ ዩጋንዳዊ መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ በአደረገ የአፍሪካ ቀንድ የደኅንነት ጥናት እና ምርምር ተቋም ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ ናቸው።
ተመራማሪው ኢትዮጵያ ያላትን የከርሰ ምድር እና የገጸ ምድር የውኃ ሀብት፤ የመልክዓ ምድር ጸጋ አድንቀው አያበቁም። ይሁንና ሕልቆ መሳፍርት ጸጋዋን ወደ ኀይል ባለመቀየሯ ዜጎቿ ከከተማ እስከ ገጠር ድረስ ምግብ አብስለው የሚጠቀሙበት ዘዴ እንደሚያሳዝናቸው እና እንደሚቆጫቸው ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ገልጸዋል።
“ቴክኖሎጂ በተራቀቀበት ዘመን ኢትዮጵያውያን እንጨት ከጫካ ሰብስበው፣ ኩበት ለቅመው እና ከሰል አያይዘው በጭስ እየታፈኑ ምግብ አብስለው ሲመገቡ ያዬ አፍሪካውያን እንደምን አያዝን? እንደምን አይቆጭ?” ይላሉ።
ተንታኙ በኀይል እጥረት ምክንያት ዘርፈ ብዙ ችግር የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን ለታላቁ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ብዙ ነገር ኾነዋል ነው ያሉት።
ገንዘባቸውን ሳይሰስቱ ለግሰዋል። ጉልበታቸውን፣ ላባቸውን ደማቸውን አፍስሰዋል ብለዋል። ሕዳሴ በኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብት ብቻ መገንባቱን ጠቁመዋል።
ሀገሪቱ ግድቡን ለመገንባት ባቀደችው እቅድ ላይ ጸንታ የቆመችው ለልማታዊ ፍላጎቷ ወሳኝ በመኾኑ ነው። ግድቡ በወንዙ መሐል የተደረደረ የኮንክሪት ክምር ሳይኾን የሚሊዮኖች ብርሃን ነውም በማለት ፋይዳውን ተናግረዋል።
የዚህ ድምር ውጤት የኾነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለፍጻሜ በቅቶ ኀይል በመስጠቱ ደስታው የአፍሪካውያን ነው ብለዋል።
የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የኀይል ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ ሀገሪቱን “የኀይል የበላይነት” ያስገኝላታል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ከራሷ ባለፈ ለጎረቤት ሀገራትም የኤሌክትሪክ ኀይል ሽያጭን በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ያስገኝላታል ብለዋል።
ቀይ ባሕርን አቋርጦ ለመካከለኛው ምሥራቅ እስያ ሀገራትም ይተርፋል ነው ያሉት።
ይህ ግድብ ጭራሽ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማያገኘው 60 በመቶ ለሚገመተው ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ኀይል ማስገኘቱ ቀናዒ አስተሳሰብ ያለውን የሰው ዘር ሁሉ የሚያስደስት ነው ብለዋል።
ሌላው መቀመጫው ኬንያ በኾነው በምሥራቅ አፍሪካ የኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ ተንታኝ ራሺድ አብዲ የሕዳሴ ግድብ ተገንብቶ መጠናቀቁ ብሪታንያ ግብጽን በቅኝ ግዛት በገዛችበት ወቅት የዓባይን ውኃ 80 በመቶ ለግብጽ ለመስጠት ያደረገችው ስምምነት ማክተሙን ያበሰረ ነው ብለውታል።
ይህም ተበዳይ ይዘገያል እንጂ የማታ ማታ አሸናፊ መኾኑን ኢትዮጵያ በታላቁ የዓባይ ወንዝ ላይ የገነባችው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሕያው ምስክር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከግብጽ የደረሰባት ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጫና፣ የጦርነት ዛቻ ሳይበግራት በልጆቿ ዓይነተ ብዙ ድጋፍ ግድቡ ተገንብቶ ተጠናቅቋል። ግድቡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማያገኘው 60 በመቶ ኢትዮጵያውያን የብርሃን ዘመንን ያመጣ ነው። አበርክቶው ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ይተርፋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን