“የተፋሰሱ የላይኛው እና የታችኛው ሀገራት ያለፉ ዘመናትን ልዩነቶች በማጥበብ በጋራ እና በመቀራረብ መሥራት ይገባቸዋል” ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ (ዶ.ር)

5

ባሕር ዳር፡ ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ተጠናቅቆ ተመርቋል፡፡ በጉባ በተካሄደው ምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ እና አሕጉር አቀፍ ድርጅት ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

 

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሀገራት መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ እና አሕጉር አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች የአጋርነት እና የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ይህ ቀን ለቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች ታላቅ የድል ቀን ነው ያሉት የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ (ዶ.ር) ናቸው፡፡

 

ዛሬ የምናስመርቀው የአንድ ነጠላ ግድብ መጠናቀቅ እና ስኬትን ብቻ አይደለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይልቁንም በቀጣናው ያለንን አቅም እና እድል ነው ብለዋል፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ውስጣዊ አቅማችንን እንድናይ፣ በአጋርነት እና በትብብር ለጋራ ተጠቃሚነት እንድንቆም ያስችላል ነው ያሉት።

 

የቀጣናውን ሀገራት በተመለከተ የሶማሊያ አቋም ግልጽ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ በጋራ መልማት፣ ማደግ እና ቀጣናዊ የትብብር ማዕቀፎቻችንን ማሳደግ ነው ብለዋል፡፡

 

ሶማሊያ ለቀጣናው ሰላም እና ብልጽግና በጋራ ለመሥራት ሁሌም ዝግጁ መኾኗን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ነው ያሉት። “የተፋሰሱ የላኛው እና የታችኛው ሀገራት ያለፉ ዘመናትን ልዩነቶች በማጥበብ በጋራ እና በመቀራረብ መሥራት ይገባቸዋል” ብለዋል በመልዕክታቸው።

 

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቀኑ ለኢትዮጵያውያን የተለየ ነው።
Next article” የሕዳሴ ግድብ አበርክቶ ለሌሎች ሀገራትም የሚተርፍ ነው” የውጭ ሀገራት የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኞች