
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም ”የማንሠራራት ቀን” ምክንያት በማድረግ የተሠሩ መሠረተ ልማቶችን ለሕዝብ አስጎብኝቷል።
በጉብኝቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የማንሠራራት ቀን አከባበር ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት ጋር በመገናኘቱ ደስታቸው እጥፍ ድርብ እንደኾነም ተናግረዋል።
ቀኑ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ነው ያሉት ከንቲባ ጎሹ የኢትዮጵውያን ሥልጣኔ የማይዋጥላቸው ኃይሎች ጥረት ቢያደርጉም ኢትዮጵያ በልጆቿ ተከብራ ኖራለች ነው ያሉት።
እርስ በእርስ ከመጋጨት በመውጣት ከፍ ያለ ልማት መሥራት እንደሚቻል የታየበት ውጤት መመዝገቡንም ነው ያብራሩት። ዛሬ የተመረቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም ሁለተኛው የዓድዋ ድል ተደግሟል ነው ያሉት። ይህም ድህነትን ለማሸነፍ እና የብልጽግና ጉዞን አይቀሬነት ማሳያ ነው ብለዋል። ሁሉም ኢትዮጵያውያንን እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደርም በለውጥ ጉዞው ዘርፈ ብዙ ለውጦች ስለመመዝገቡም ነው ያስረዱት። ወቅታዊ ሁኔታው ቢያስቸግርም ልማቱንም በማስቀጠል ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። ለዚህም ለልማት እና ለሰላም እገዛ ያደረጉትን እና መስዋዕትነት የከፈሉትንም ጭምር አመሥግነዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ከ2011 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ተጀምረው ያደሩትን ፕሮጀክቶች የማጠናቀቅ፣ አዳዲስ የመጀመር እና የማጠናቀቅ ሥራ ሠርቷልም ብለዋል።
17 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ሥራ መጠናቀቁን፣ የቄራ ግንባታ በቀጣይ ዓመት አገልግሎት እንደሚሰጥ፣ በባሕር ዳር ከተማ 30 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት በመሠራት ጣና ሐይቅ እና ባሕር ዳርን የበለጠ ማስተሳሰር መቻሉን እና የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች መገንባታቸውንም ገልጸዋል። ከዚህ በኋላ ተጀምሮ የሚቀር ፕሮጀክት እንደማይኖርም ነው የጠቆሙት።
የመልካም አሥተዳደር ችግርን ለመፍታት በስማርት ሲቲ ፕሮጀክት የደኅንነት ካሜራ መገጠሙን፣ ለፈጣን አገልግሎት ዲጂታላይዜሽን መጀመሩን እና የመሬት ቆጠራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህም የሕዝቡ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች እንደሚፈቱም አስገንዝበዋል።
የልማት እና የማንሠራራት ጉዞ በታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ብቻ ሳይኾን በእያንዳንዱ መንደር ተጀምሯልም ነው ያሉት። ለዚህም የከተማው ሕዝብ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በጉብኝቱ የተሳተፉት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ኮማንደር አስማረ ሰጠኝ የከተማዋ ልማት የበለጠ የተዋበች እና ተወዳዳሪ የሚያደርጋት መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የተናገሩት።
በታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ መሥራታቸውን እና መጎብኘታቸውን የገለጹት ኮማንደር አስማረ ግድቡ አዲስ ትውልድ መፍጠሩን አብራርተዋል። በቀጣይም መሰል ልማት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ እና ጎብኝ ወጣት ዘላለም አሸናፊ የተሠሩት መሠረተ ልማቶች ከተማዋን የበለጠ የምታምር እንዳደረጋት ገልጿል። በቀጣይም በሌሎች የከተማዋ ክፍሎች ልማቱ እንዲሰፋ ነው የጠየቀው።
የማንሠራራት ቀንም በሰላም እጦት ምክንያት ከነበረው ድባቴ የሚወጣበት፣ መልካም ተስፋ የሚታይበት እና ለመጭው አዲስ ዓመትም ብሩህ ተስፋ የሚሰነቅበት ነው ብሏል።
ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አንጡራ ሃብት የገነቡት የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ከችግራቸው ሊያዎጣቸው በመመረቁ መደሰቱን ጠቁሟል።
ዘጋበ:- ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!