
ባሕር ዳር፡ ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ተጠናቅቆ እየተመረቀ ነው፡፡ በጉባ እየተካሄደ በሚገኘው ምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ እና አሕጉር አቀፍ ድርጅት ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሀገራት መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ እና አሕጉር አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች የአጋርነት እና የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እያስተላለፉ ነው፡፡ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የኬኒያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ (ዶ.ር) የግድቡ ግንባታ የምህንድስና ጥበብ ብቻ ሳይኾን የአፍሪካ ሀገራትን የማደግ እና የመበልጸግ መሻት በግልጽ የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት ለጋራ ራዕያችን ወንድማዊ ትብብርን ማጠናከር እንዳለብን ያመላከተ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ “ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የፓን-አፍሪካኒዝም መንፈስ መገለጫ ነው” ብለውታል፡፡ ዛሬ መላው አፍሪካውያንም መሰል ታላላቅ ፕሮጀክቶችን መሥራት እንደምንችል ትምህርት የወሰድንበት ነው ብለዋል፡፡
ግድቡ አፍሪካውያንን በኤሌክትሪክ ኃይል የሚያስተሳስር እና የታዳሽ ኃይል ተደራሽነትን የሚያስፋፋ ፕሮጀክት መኾኑን የገለጹት ፕሬዝዳንት ሩቶ በአሕጉሩ 600 ሚሊየን የሚደርስ ሕዝብ የኃይል አቅርቦት የለውም ነው ያሉት፡፡ ይህንን የተዛባ የአኗኗር ዘይቤ ለመቀየር እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዓይነት ፕሮጀክቶች ፋይዳቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አሕጉሪቷ ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት እንዳላትም አንስተዋል፡፡ በኃይል ኢንቨስመንት ላይ በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ፕሬዝዳት ሩቶ ኬኒያ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከመነጨው ኃይል ለመግዛት ትፈልጋለች ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!