
ከሚሴ፡ ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በርካታ ውጣውረዶችን በማለፍ ለምረቃ የበቃዉን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት በማድረግ በተለያዩ ከተሞች የበዓሉ የደስታ መልዕክት በአደባባይ እየተላለፈ ነው።
ይህንንም ተከትሎ የከሚሴ ከተማ እና አካባቢዋ ነዋሪዎችም በከተማዋ አደባባዮች በመውጣት ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። ነዋሪዎቹ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከዛሬ 14 ዓመት በፊት ሲጀመር ጀምሮ ቦንድ በመግዛት ድጋፋቸውን ሲያደርጉ እንደነበር ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል አቶ ኢብራሒም መሐመድ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የ14 ዓመታት ውጣውረዶችን በመሻገር ለምረቃ ሲበቃ በማየታቸው እና የዚህ ታላቅ ታሪክ አካል በመኾናቸው ደስታቸው እጥፍ መኾኑን ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድቡን ለማደናቀፍ በርካታ ኃይሎች ቢሞክሩም እንደሀገር ጸንተን በመታገላችን ለዛሬ በቅተናል ብለዋል።
የሕዳሴ ግድብ በራስ አቅም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፈውበት የተሠራ ሀገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክት መኾኑን ገልጸዋል።
መላው ኢትዮጵያውያን የማይቻለውን ችለን ለዓለም ያሳየንበት ነው ብለዋል። በቀጣይም አንድነታችንን አስጠብቀን ልንሠራ ይገባል ነው ያሉት።
የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሸሪፍ ቃሲም ሕዳሴ ከህፃናት እስከ አዛውንቶች ያዋጣንበት የይቻላል መንፈስ ማሳያ ነው ብለዋል። በቀጣይም የሀገራችንን ብልጽግና ለማረጋገጥ በኹሉም ዘርፍ በጋራ ቆመን ልንሠራ ይገባል ነው ያሉት።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በላባቸውና በደማቸው የፃፉት አኩሪ የድል ታሪክ መኾኑን ተናግረዋል።
የሀገራችን ብልጽግና አይቀሬ መኾኑን ያሳየንበት ነው ያሉት አሥተዳዳሪው በቀጣይም አንድነታችንን አጠናክረን ለሀገራችን ማንሠራራት ተባብረን ልንሠራ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!