
ደብረ ማርቆስ: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጳጉሜን አራት የማንሠራራት ቀን “ዘላቂ ልማት ለሀገራዊ ማንሠራራት” በሚል መሪ መልዕክት በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተከብሯል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ አበባው ግዛቸው የማንሠራራት ቀንን ኢትዮጵያ በራሷ አቅም በመልማት እድገትን ለማረጋገጥ እየታጋች ባለችበት ወቅት ማክበራችን ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።
ቀጣይም በኅብረት ሀገሪቱ ያላትን ሃብት በመጠቀም ለሕዝቦች ተጠቃሚነት የምንተጋበት ሊኾን ይገባል ነው ያሉት።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ ትዕግስት ልየው የማንሠራራት ቀን ሲከበር እንደ ሀገር የጋራ መግባባትን የፈጠረው የሕዳሴ ግድብን ሠርተን ያጠናቀቅንበት በመኾኑ ትልቅ ትርጉም ያለው ብለዋል።
የማንሠራራት ቀን ሲከበር እንደ ሕዳሴ ግድብ ሁሉ በሌሎችም የልማት ሥራዎችን በኅብረት በመቆም የሀገርን ገጽታ ለመገንባት በማለም መኾን አለበት ነው ያሉት።
“የዘመናት ቁጭት የኾነው የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለቀጣይ ልማቶችም ስንቅ የሚኾን ነው” ብለዋል።
የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎችም ቀኑ የዘመናት ሕልም እና ቁጭት የኾነው የሕዳሴ ግድብን በኅብረት ሠርተን በማጠናቅ ለወደፊት የልማት ሥራዎች ትልቅ አቅም የምንፈጥርበት ነው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!