“በደቡብ ሱዳናዊያን ዘንድ ኢትዮጵያዊያን ጎረቤት ብቻ ሳይኾኑ የጋራ ፍላጎት ያላቸው ወንድማማች ሕዝቦች ጭምርም ናቸው” ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት

4

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ተጠናቅቆ እየተመረቀ ነው፡፡ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ እና አሕጉር አቀፍ ድርጅት ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

 

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሀገራት መሪዎች የአጋርነት እና የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እያስተላለፉ ነው፡፡

 

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኃይል ምንጭነቱ በላይ የኢትዮጵያዊያን የአንድነት ምልክት እና የቀጣናው ሀገራት ትስስር ገመድ ነው ያሉት የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ናቸው፡፡ ይህ ግድብ እውን እንዲኾን ኢትዮጵያ የበዛ ዋጋን ከፍላለች ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህ ቀን የኢትዮጵያ እና የቀጣናው ሀገራት የኩራት ቀን ነው ብለውታል፡፡

 

ከዚህ ግድብ ኃይል ብቻ ሳይኾን ቀጣናዊ እድገትን፣ ሀገራዊ ተስፋ እና ለልጆቻችን የሚተርፍ ገፀ-በረከት እናገኝበታለን ያሉት ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ደቡብ ሱዳን ከግድቡ ኃይል ለመግዛት የሚያስችል ስምምነት እንደምትፈራረም ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ብለዋል፡፡

 

ግድቡ ለደቡብ ሱዳናውያን የገጠር ሰፈሮች፣ ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች የኃይል ምንጭም ኾኖ ያገለግላል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ቀጣናውን በጋራ ለማልማት ሚናው የጎለ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡

 

“በደቡብ ሱዳናዊያን ዘንድ ኢትዮጵያዊያን ጎረቤት ብቻ ሳይኾኑ የጋራ ፍላጎት ያላቸው ወንድማማች ሕዝቦች ጭምርም ናቸው” ያሉት ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የሚያጋጥሙን መሰናክሎች እና ፈተናዎች በጋራ በመቆም የሰላም፣ የእድገት እና ብልጽግና ዕድሎች እናደርጋቸዋለን ነው ያሉት፡፡

 

ዘጋቢ:- ታዘብ አራጋው

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እኛ ኢትዮጵያውያን አካላችን ሞቶ የማይሞት አሻራ ለማኖር የምንተጋ ሕዝቦች ነን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) 
Next articleየታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ በመመረቁ ኩራት እንደተሰማቸው የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።