
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የምረቃ ሥነ ሥርዓት የሀገር ውስጥ እና የውጭ እንግዶች በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ታሪክ ሰምተናል፤ ታሪክ አይተናል፤ ታሪክ ተምረናል፤ ዛሬ ደግሞ ፈጣሪ የመረጠው ትውልድ መኾን ስለቻልን ታሪክ ሠርተን እና ታሪክ ላይ ቆመን ለማውራት በቅተናል ብለዋል።
ሕዳሴ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለጥቁር ሕዝቦች በሙሉ ታሪክ ኾኖ የሚኖር ታላቅ ገድል ስለመኾኑም ተናግረዋል።
ዓባይ እግር እንጅ አፍ ስላልነበረው ኢትዮጵያውያን በልዩ ልዩ መንገድ ለዓባይ አፍ ኾነው ሲናገሩለት ኖረዋል፤ ዛሬ ግን ዓባይ አፍ አውጥቶ ራሱ መናገር ችሏል ነው ያሉት። ሕዳሴን በቪዲዮም፣ በፎቶ ወይም በንግግር መግለጥ አይቻልም፤ ማንም ኢትዮጵያዊ ይህንን ግድብ በዓይኑ ሳያይ ማለፍ እንደሌለበት ምኞቴ ነው ሲሉም ተናግረዋል። ምክንያቱም በዓይኑ ያየ ሰው ብቻ ነው የሕዳሴን ልክ መረዳት የሚችለው ብለዋል።
በጥቁር ዘር ታሪክ የመጀመሪያው ታላቅ ሥራ ሕዳሴ ነው፤ መላው ጥቁር ሕዝብ እየመጣ ይመልከተው ሲሉም ጋብዘዋል።
“ሕዳሴ የትላንት ቁጭት ማሰሪያ፣ የመጭው ንጋት ማብሰሪያ ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ንጋት ሐይቅ 74 ትሪሊዮን ሊትር ውኃ ይዟል፤ ወደ ገንዘብ ተተምኖ በሊትር አንድ ብር ብቻ ውኃ ቢሸጥ እንኳን 74 ትሪሊዮን ብር ይኾናል ሲሉ የግድቡን የገዘፈ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ቀለል ባለ ምሳሌ አስረድተዋል።
ሕዳሴ የኢትዮጵያን ጥልቅ ጨለማ እና እንቅልፍ ያነቃ በመኾኑ ሐይቁ “ንጋት” ስለመባሉም ተናግረዋል። ሕዳሴ የኢትዮጵያን የልመና እና የእንጉርጉሮ ዘመን የሚዘጋ እና እንደልኳ የምትለካበትን ዘመን ፊት ለፊቷ የሚዘረጋ ስለመኾኑም አብራርተዋል። ያኔ ኢትዮጵያ ተረጅነቷ አብቅቶ ረጅ ትኾናለች ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ የማንሠራራት ዘመን ከእኛ ጋር የተገኙ ሁሉ በትውልዶቻችን ሁሉ መመስገን ብቻ ሳይኾን ሀገራችን ከጸጋዋ፣ ከተስፋዋ እና ከልምዷ እንደምታካፍላቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
የታችኛው ተፋሰስ ወንድሞቻችን፣ የኑቢያ ወንድሞቻችን፣ ኢትዮጵያ ሕዳሴን የሠራችው ለመበልጸግ፣ አካባቢውን በብርሃን ለመሙላት እና የጥቁር ሕዝቦችን ታሪክ ለመቀየር እንጅ ወንድሞቿን ለመጉዳት ግን በፍጹም ሊኾን አይችልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ስጋት የሚያድርባቸው ወንድሞች ካሉም ኢትዮጵያ በፍጹም የነሱን ሀቅ የማትነካ መኾኑን ይወቁ ብለዋል።
የወንድሞቻችን እርሃብ እና ችግር የኛም ችግር ነው፤ እኛ ተጠቅመን ሌሎችን የመጉዳት መሻት የለንም፤ ለወደፊት በምንሠራቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶችም አብረን መቆም ነው ያለብን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያውያን ገደሉን ተሻግረናል፤ ስለ ሕዳሴ እና ስለ ንጋት በመናገር ጊዜ አናባክንም፤ ይህንን ፋይል ዘግተን በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እንሠራለን ብለዋል።
ለሰላማዊ ዓላማ የሚውል የኒውክሌር ፕላንት በቅርቡ ትሠራለች፤ በአፍሪካ ግዙፉን የአየር መንገድ እንገነባለን፤ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የመጀመሪያው የጋዝ ፋብሪካ ይመረቃል፤ ለዘመናት ስንመኝ የነበረው የነዳጅ ሕልማችንን እውን የሚያደርግ የማጣሪያ ግንባታም ሥራ እንደሚጀመር ገልጸዋል።
በድምሩ ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብት የሚፈስባቸው እና የአፍሪካን ልጆች ጭምር ቀና የሚያደርጉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ከፊታችን እየጠበቁን ነው ሲሉም አብስረዋል። ለዚህም የሕዳሴን ንጋት ተከትለን በጋራ ቆመን መሥራት አለብን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ የታሪክ እጥፋት እና የማንሠራራት ዘመን ዛሬ ታውጇል፤ ተባብረን ኢትዮጵያን እናቅና” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። “እኛ ኢትዮጵያውያን የማይሞት ስም እንጅ የማይሞት አካል የለንም፤ አካላችን ሞቶ የማይሞት ስም ለማስቀረት እና አሻራ ለማኖር የምንተጋ ሕዝቦች ስለኾን ከኛ ጋር መጋጨት ሳይኾን መስማማት ብቻ ነው የሚያዋጣ” ሲሉም ኢትዮጵያን ለሚጠሉት ሁሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!