
ደብረ ብርሃን: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ ዛሬ ተመርቋል።
ይህ ስኬት በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ሀገራት ላሉ ኢትዮጵያውያን እና ወዳጅ ሕዝቦች ትልቅ የደስታ ስሜትን አጎናጽፏል።
አሚኮ በደብረ ብርሃን ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎችም የጽናት፣ የአልበገር ባይነት እና የይቻላል መንፈስ የታየበት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዚህ ዘመን ለዚህ ክብር መብቃቱ እንዳስደሰታቸው ነው ሃሳባቸውን ያጋሩት።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት በውጫዊ እና በውስጣዊ ጫና ውስጥ ያለፈ መኾኑ ኢትዮጵያውያን ምንም ጫና ቢበዛባቸው ከስኬት እና ዓላማቸውን ከማሳካት የሚያግዳቸው እንደሌለ ማሳያ ነው ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለፍሬ ደርሶ ዛሬ ለመመረቅ የበቃው ኢትዮጵያውያን በሙሉ በገንዘባቸው፣ በሃሳባቸው፣ በላባቸው እና በዕውቀታቸው ተረባርበው እንደኾነም ተናግረዋል።
ይህ አንድነትም ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ብትጀምርም ማጠናቀቅ አትችልም ላሉ ባዕዳን መቻልን ያሳየችበት እንደኾነም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣይ መሰል ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደምትችል ማሳያ እንደኾነም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ደጀኔ በቀለ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!