የማንሰራራት ቀንን በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምረቃ ዕለት ማክበር የተለየ ስሜትን እና ተስፋን ይፈጥራል፡፡

16

ደሴ: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም የማንሰራራት ቀን በደሴ ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡

 

በዝግጅቱ “ዘላቂ ልማት ለሀገራዊ ማንሰራራት፣ የቱሪዝም ልማት ለኢትዮጵያ ብስራት፣ የከተሞች ሁለንተናዊ ልማት ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” የሚሉ መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡

 

ነዋሪዎች በደሴ ከተማ በቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ፣ ጤና እና የትራንስፖርት ዘርፎች የተመዘገቡ ለውጦች አበረታች እና ለከተማዋ እመርታ ወሳኝ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡

 

የደሴ ከተማ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ትዕግስት አበበ ቱሪዝምን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እና ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡

 

ቱሪዝሙ ብቻውን ለውጥ ስለማያመጣ የአገልግሎት ዘርፉንም አብሮ ማሳደግ ይገባል ያሉት ኀላፊዋ ከአምስት በላይ የሚኾኑ ትላልቅ ሆቴሎች በከተማ ደረጃ ለመገንባት ፍቃድ ጠይቀው የክልል ምላሽ እየተጠበቀ እንደኾነም አስረድተዋል።

 

በተጨማሪም አገልግሎት እየሰጡ የነበሩ ስድስት ሆቴሎች ከማስፋፊያ ቦታ እና ከሌሎች ችግሮች አንጻር ሲያነሷቸው የነበሩ ጥያቄዎች እንዲፈቱ መደረጉንም ተናግረዋል።

 

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ሰይድ የሱፍ ዕለቱ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እየተመረቀ ያለበት በመኾኑ የላቀ ስሜትን የፈጠረ መኾኑን አንስተዋል፡፡

 

ኢትዮጵያ ብዙ ፀጋ ያላት እና ለዘመናት ይህንን ሃብቷን ሳትጠቀም ቆይታ አሁን ላይ እንደ ሕዳሴ ግድብ አይነት የጋራ መተባበርን የሚጠይቁ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የዕድገት ጉዞዋ እንዲፋጠን እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

 

የማንሰራራት ቀን በዚህ ሁኔታ ማክበር የተለየ ስሜትን እና ተስፋን እንደፈጠረባቸውም ነው የጠቆሙት፡፡

 

ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር የተመዘገበው ትሩፋት በደሴ ከተማ ደረጃም ብዙ የስኬት ጉዞዎች የታዩበት ነው ብለዋል።

 

በመሠረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪ እና በቱሪዝም ዘርፉ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡

 

ያለፉት ጊዜያት ለውጦችን መሠረት በማድረግ በቀጣይ ዓመት ከተስፋ ወደሚጨበጥ ለውጥ መሸጋገር እንዲቻል እና ኢትዮጵያውያንም ወደ ነበሩበት ከፍታ እንዲመለሱ በትብብር እና በአንድነት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

 

ዘጋቢ:-ደጀን አምባቸው

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በጋራ መሥራትን ያሳየ የዘመኑ ትሩፋት ነው፡፡
Next articleታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጽናትና አልበገር ባይነት የታየበት ነው።