
ፍኖተ ሰላም: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ በመላው ኢትዮጵያውያን ኅብረት እና ተሳትፎ የተጠናቀቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለምረቃ በቅቷል።
በዚህም መላው ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
አስተያየታቸውን ያጋሩን የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር የሕዝብ ቅሬታ ሰሚ እና አሥተዳደራዊ ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጎጃም አበረ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የወደፊት እድገታችንን የሚጠቁም ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
በኅብረት ሠርተን ማደግ እና መለወጥ እንደምንችል ያሳየ እና ለኢትዮጵያውያን የማንቂያ ደወል የኾነ እንደኾነም ነው የገለጹት።
“ግድቡ የእናቶች መቀነት አሻራ ውጤት ነው” ብለዋል።
ሌላው አስተያየታቸውን ያጋሩን በፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ብርሃኑ ጋሹ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በጋራ ተባብረን ከሠራን ሁሉንም ችግሮቻችንን መፍታት የምንችል መኾኑን ያሳየ አንጡር ሃብታችን እንደኾነ ነው የገለጹት።
የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር 02 ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እምቅድመ ዓለም አበበ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ማየት ልጅ ወልዶ ለወግ ማዕረግ እንደማድረስ ነው ብለዋል።
ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በር የከፈተ የልማት ሥራ መኾኑንም ተናግረዋል ።
ግድቡ ለሌሎች የልማት ሥራዎች በር የከፈተ በመኾኑ ልክ እንደ ሕዳሴ ግድቡ ያለንን እምቅ ሃብት በመጠቀም መሥራት እንደሚያስፈልግም አስተያየት ሰጭዎቹ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!