ኢትዮጵያ የማንሠራራት ዘመን ላይ መኾኗን የሚያሳዩ ሥራዎች ተሠርተዋል።

10
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጳጉሜን 4 ” የማንሠራራት ቀን” በአማራ ክልል በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።
በሥነ ሥርዓቱ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)ን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ልዩ አማካሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) የአማራ ክልል የማንሠራራት ዘመንን የሚያሳዩ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል። በክልሉ ሩቅ መንገድ የሚያስጉዙን እምቅ አቅሞች አሉ ነው ያሉት። የሕዝባችንን እድገት ለማረጋገጥ እና ኢትዮጵያ ያሰበችውን የእድገት ጉዞ ለማሳካት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ሕዝብን ከድህነት ለማውጣት የሚያስችል ዕቅድ ታቅዶ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል። የክልሉ መሪዎች እና ሕዝቡ የታቀደው የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ እንዲሳካ በትኩረት እንዲሠሩም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኀይሌ አበበ ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን የማንሠራራት ዘመን የሚያበስሩ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ለውጥ ከተጀመረ ወዲህ በማዕድን ዘርፉ በርካታ የለውጥ ሥራዎች መታየታቸውን ገልጸዋል። ከለውጡ በኋላ የማዕድን ዘርፉን ለሀገር ብልጽግና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል። ማዕድን የሀገር ብልጽግና መሠረት መኾኑንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ከፍተኛ የኾነ የማዕድን ሀብት እንዳለውም ገልጸዋል። ክልሉ በዓለም በእጅጉ የሚፈለጉ ማዕድናት የሚገኙበት እንደኾነም ተናግረዋል። እስካሁን የማዕድን ሀብቱን በቴክኖሎጂ በመደገፍ እንዳልተሠራበት ገልጸዋል። በማዕድን ዘርፉ በትኩረት ከሠራን ክልሉን በአጭር ጊዜ ማስፈንጠር እንችላለን ነው ያሉት።
የአማራ ክልል የማዕድን ሀብትን ለውጭ ገበያ እያቀረበ መኾኑንም ተናግረዋል። የማዕድን ዘርፉ በትኩረት ከተሠራበት ሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ የውጭ ምንዛሬን ያሳድጋል፤ ከውጭ የሚገባ ምርትንም ያስቀራል ነው ያሉት።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት ግብርናው በብዙ መንገድ መለወጡን ተናግረዋል። የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለግብርና የሚመች የአየር ንብረት እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ የሌማት ትሩፋት እምርታዊ ለውጥ አምጥተዋል ነው ያሉት። የበጋ ስንዴ በምግብ ራስን ለመቻል በሚሠራው ሥራ ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረገ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ግብርናውን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበው ለውጥ የማንሠራራት ዘመን ላይ መኾናችንን የሚያሳይ ነው ብለዋል። በሁሉም ዘርፍ ኢትዮጵያ የማንሠራራት ዘመን ላይ መኾኗን የሚያሳዩ ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል የ25 ዓመታት የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ ወደ ሥራ መግባቱን ያመላከቱት ኀላፊው አዲሱን ዓመት በልዩ ሁኔታ ነው የምንቀበለው፤ ምክንያቱም በአሮጌው ዓመት ዓይን ገላጭ ሥራዎች ተሠርተዋልና ነው ያሉት።
የክልሉ ሕዝብ ዕቅዱ እንዲሳካ ርብርብ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article“አድዋ እና ዓባይ”
Next articleበደብረብርሃን ከተማ “የማንሰራራት” ቀንን ምክንያት በማደረግ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተካሄደ።