
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያውያን የገንዘብ፣ የላብ፣ የእንባ፣ የደም እና የሕይወት መስዕዋትነት ፍሬ ዛሬ እውን ኾኗል። ይሄ ሁሉ በአንድ ላይ እና ያለስስት የተከፈለበት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውጣ ውረዶችን አልፎ ለሪቫን መቁረጥ ሥነ ሥርዓት በቅቷል።
መላ ኢትዮጵያውያንም የመቻላቸው ምልክት ለኾነላቸው የሕዳሴ ግድብ ደስታቸውን እየገለጹ ነው።
በባሕር ዳር ከተማ ደስታቸውን ሲገልጹ ያገኘናቸው ነዋሪዎችም “ሕዳሴ የሀገራችን የከፍታ ጅማሮ እና የትብብራችን ፍሬ ያየንበት ነው” ብለዋል።
ደስታቸውን ለአሚኮ ከገለጹት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ የምስራች አበጀ ግድቡ በመመረቁ የተሰማቸውን የደስታ መጠን ሊገልጹት የማይቻል ስለመኾኑ ተናግረዋል።
ዓባይ ከዚህ በፊት የሙዚቃ እና የግጥም ማድመቂያ ብቻ የነበረ፤ አሁን ግን በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት ወደ ተጨባጭ ጥቅም የተቀየረ የደም እና የላብ ውጤት ነው ብለዋል።
የሕዳሴው ግድብ ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱ ኢትዮጵያን ከችግር የሚያወጣ እና የሀገርን የዕድገት መንገድም የሚጠርግ እንደሚኾን ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን በጉጉት ሲጠብቁት ለነበረው ቀን በመድረሳቸውም የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዓባይ መተባበራችን የወለደው የፍቅር ምልክት እና መተሳሰሪያችን ነው ያሉት ነዋሪዋ አሁንም ቢኾን በጋራ በመቆም ሌሎችንም ትላልቅ ፕሮጀክቶች ማለም እና መገንባት እንደሚገባ ነው የገለጹት።
ሌላው ወጣት ሰለሞን ታምሬ የተባለ ነዋሪም የሕዳሴው ግድብ ተጠናቅቆ ለምርቃት በመብቃቱ የተሰማውን ደስታ ገልጾ ለመላ ኢትዮጵያውያንም የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
“ግድቡ የኔም አሻራ ያለበት ነው፤ የኔን ትውልድ እና መጭውን ትውልድም በኢኮኖሚ ከፍ የሚያደርግ እንደኾነም ተስፋ አለኝ” ብሏል።
ግድቡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘው የገነቡት ነው፤ ከዚህ ልምድ በመውሰድም የበለጠ በአንድነት መቆም እና ለተጨማሪ መሰል ፕሮጀክቶች መዘጋጀት ይገባል ሲልም ሃሳቡን ገልጿል።
የሕዳሴው ግድብ ድሃ እናት መቀነቷን ፈትታ እና ሕጻናትም ከሻይ ሳንቲም ቀንሰው በመለገስ የገነቡት የትብብር ተምሳሌት ነው ያለችን ደግሞ ወጣት ትበይን ባንትይሁን የተባለች ነዋሪ ናት።
ይህ ግድብ እንኳንስ ለኢትዮጵያውያን ለአፍሪካም ጭምር ትምህርት የሰጠ የከፍታ ምልክት ስለመኾኑም ገልጻለች።
ኢትዮጵያውያን በዓባይ ላይ ያሳዩትን ትብብር የበለጠ በማሳደግ አሁንም እጅ ለእጅ በመያያዝ ሌላ የዕድገት መሠረት የኾኑ ፕሮጀክቶችን ማሰብ እና ማሳካት ይገባል ስትልም ገልጻለች።
የሕዳሴው ግድብ ለሌላ ትልልቅ ሥራዎች የሚያነሳሳ እና የተስፋ ምንጭ ነውም ብላለች።
“በዓባይ ጉዳይ ያለመለያየት ሠርተን ውጤት አይተናል፤ የትብብራችንን ፍሬ በማየታችንም እንኳን ደስ ያለን” በማለትም ደስታዋን ገልጻለች።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!