
ገንዳ ውኃ: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን መመረቅ አስመልክቶ የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪዎች እና መንግሥት ሠራተኞች ሃሳባቸውን ለአሚኮ ሰጥተዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጋሻው አራጋው የ14 ዓመታት የጽናት ጉዞውን ጨርሶ ለኢትዮጵያውያን ሕዝብ ችግር ፈንጣቂ የኾነው የሕዳሴ ግድብ በመመረቁ ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ያስተሳሰረ እና የሀገር ብልጽግና የሚረጋገጥበት ማሳያ መኾኑን አይተናል ነው ያሉት። “ሕዳሴ በይቻላል የሥራ መንፈስ የደፈርነው ፕሮጀክት እንደኾነ “ገልጸዋል። ብዙ ጠላቶችን አንገት አስደፍተን ያሳፈርንበት የጀግንነት አርማ ነውም ብለውታል።
በቱሪዝም ዘርፉም ግድቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ እንደምትችል ለዓለም ሀገራት ያሳየንበት እና ያስመሰከርንበት ታሪክ ነው ብለዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቡና ሻንቆ ኢትዮጵያዊያን ስንተባበር እና ስንደጋገፍ መሥራት እንደምንችል በሕዳሴው ግድብ ጀግንነታችን አሳይተናል ብለዋል።
የሕዳሴው ግድብ በጭስ እና በጨለማ ለሚሰቃዩ እናቶች ብርሃንን፣ ተስፋን እና ደስታን ይዞ የመጣ ዕንቁ ሃብታችን ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ግድቡ ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በዲፕሎማሲያዊ ሁነቶች ከፍ የሚያደርግ መኾኑንም ተናግረዋል።
ሌላዋ አስተያየት ሰጭ ወይዘሮ ተስፋ ልየው ናቸው። ሕዳሴ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚጓዝበት የስኬት መንገድ መኾኑን ገልጸዋል።
ግድቡ ለብዙ ወጣቶች በዓሳ ማስገር ሥራ የሥራ ዕድል የፈጠረ እና ቀጣይም በመስኖ ልማት ሥራዎች ለሌሎች ወጣቶች ሥራ እንደሚፈጥርም ነው የተናገሩት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!