
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዲፕሎማሲ በውጭ መንግሥታት ወይም ድርጅቶች መካከል ያለውን ልዩነት በውይይት፣ በድርድር እና ሌሎች ሰላማዊ መንገዶችን በመጠቀም ተጽዕኖ ማሳረፍ የሚያስችል ጥበብ የተሞላበት የግንኙነት አግባብ ነው፡፡
አንድ መንግሥት ከሌላው ዓለም ጋር ለሚኖረው ግንኙነት ያስቀመጠውን ግብ እና ስትራቴጂ የሚወክል የውጭ ፖሊሲ ዋነኛ መሣሪያ ተደርጎም ይወሰዳል፤ ዲፕሎማሲ።
የሀገሮች ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች፣ ውሎች፣ ትብብሮች እና ሌሎች የውጭ ፖሊሲ መገለጫዎችም ፡በብዛት የዲፕሎማሲያዊ ድርድሮች እና ሂደቶች ውጤት ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ላይ አብዛኛው የዲፕሎማሲ ሥራ በየሀገሮቹ መንግሥታት ዘንድ ዕውቅና ባላቸው ልዑካን እና አምባሳደሮች ተወስኖ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶች በኩል ይካሄዳል፡፡
የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ሥራን የበለጠ ለማጠናከር በመንግሥት እውቅና የተሰጣቸውን ተቋማት ከማጠናከር ባለፈ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ተበታትኖ የሚኖረውን ዜጋ በማሰባሰብ በዲፕሎማሲያዊው ሥራ እንዲሳተፍ እና እያንዳንዱ ዜጋ የሀገሩ አምባሳደር እንዲኾን መሥራትም ሌላው አማራጭ ነው፡፡
ከአንድ አምባሳደር ባልተናነሰ መልኩ ያለምንም ክፍያ የዲፕሎማሲ ሥራ የሠሩ የቁርጥ ቀን ኢትዮጵያውያን ባለፉት ዓመታት ታይተዋል። ከእነዚህ ውስጥ መሐመድ አል አሩሲ ተጠቃሽ ነው፡፡
መሐመድ አል አሩሲ ከ300 ጊዜ በላይ በአረብ ሚዲያ በተለይም በአልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ በመቅረብ ግብጽ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ የምታራምደውን የተሳሳተ ዕይታ በአረብኛ ቋንቋ ለዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ያስረዳ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡
መሐመድ አል አሩሲ እንዳለው ግብጾች ስለዓባይ ለሕዝባቸው እና ለአረቡ ዓለም የተሳሳተ መረጃ ሲያቀርቡ ኖረዋል ብለዋል፡፡ ይህንን የተሳሳተ መረጃ ለመቀልበስ በመንግሥት የተመደበ አምባሳደር ሥራ ብቻ ሳይኾን ኢትዮጵያዊ መኾን ብቻ በቂ መኾኑንም ተናግሯል፡፡
ኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክ ያላት ሀገር እንደኾነች የገለጸው መሐመድ አል አሩሲ በእስልምና ሃይማኖትም ትልቅ ቦታ ያላት የቃል ኪዳን ሀገር መኾኗን አንስቷል፡፡
ስለ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በምከራከርበት ወቅት ከሌላ ሀገር መጥቶ እንጂ ኢትዮጵያዊ አይደለም ይላሉ፤ እኔ ግን የምከራከረው ኢትዮጵያዊ ኾኜ የሀገሬን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው ሲልም ተደምጧል፡፡ ኢትዮጵያውን ለጎረቤት ሀገሮች ሰላም እና ዕድገትን እንጅ ምቀኝነትን አንመኝም፤ እኛ የዓባይ ልጆች አንድ ሕዝቦች ነን ብሏል፡፡
መሐመድ አል አሩሲ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ በሚከራከርበት ወቅት የግብጽ ወንድሞቻችን የሚለውን ቃል እንደሚጠቀምም አንስቷል፡፡ ይህም የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ዓባይ ያስተሳሰራቸው የዓባይ ልጆች መኾናቸውን እና በጋራ መልማት እንደሚገባቸው ለማሳየት እንደኾነ ለአልጀዚራ እና ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጠው ቃለ መጠይቅ አንስቷል፡፡
ስለ ሕዳሴ ግድብ እውነታ በዲጅታል በማቅረብ እና የግብጾችን ሴራ በማጋለጥ ዓለም በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያውያን እንዲረዱት በማድረግ ትልቅ ሥራ ከሠሩ አምባሳደሮች ኡስታዝ ጀማል በሽር ሌላኛው ነው።
ግብጾች ከ200 በላይ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እና ዲጂታል ሚዲያዎችን ተጠቅመው ስለ ኢትዮጵያ እና ሕዳሴው ግድብ ግንባታ የተሳሳቱ ዜናዎችን፣ ፕሮግራሞችን እና መረጃዎችን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንደሚያሠራጩ ገልጿል።
የሕዳሴው ግድብ፤ የግብጽን የውኃ ድርሻ በመቀማት ብሔራዊ የደኅንነት ሥጋት እንደሚፈጥር አድርገው ሀሰተኛ መረጃ እንደሚያሰራጩ ነው የተናገሩት።
በዲጂታል ሚዲያ የዓረቡ ዓለም እውነታውን እንዲረዳ፣ የሕዳሴው ግድብ የሚይዘው ውኃ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉዳት እንደማያስከትል እውነታውን በማስረዳት እና በርካታ የዓረብ ሀገራት ለሕዳሴው ግድብ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ማድረግ መቻሉን ኡስታዝ ጀማል ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!