
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓባይ ለኢትዮጵያውያን ወንዝ ብቻ አይደለም። ዓባይ ለኢትዮጵያውያን ዜማ፣ እንጉርጉሮ፣ እሴት ኾኖ ዘመናትን ዘልቋል። እረኛው በዋሽንቱ፣ አዝማሪው በመሰንቆው፣ ሽማግሌዎች በምርቃታቸው፣ ዘፋኞች በድምጻቸው፣ ገጣሚዎች በስንኛቸው ዓባይን ሲያወድሱት፣ ሲያነሱት፣ ሲያሞግሱት ኖረዋል።
ዓባይ ሀገሩን እንደማያውቅ በመሀል ሀገር እየተገማሸረ የባዕዳን ሀገርን መርጦ በማናለብኝነት ሲኮበልል ኖሯል። ያለፉት ትውልዶች ብዙ ተመኝተው ዓባይን በቤታቸው ሊያስቀሩት፣ ከባዕድ ሀገር ግዞት ነጻ ሊያወጡት ጥረዋል ግን ጉልበታሙ ዓባይ ሳይቀመስ እስከዚህ ትውልድ ደርሷል።
መክሮ የማይታክት፣ ገጥሞ የማይሸነፍ፣ ሠርቶ የማይደክም ሁሌም ተስፈኛ እና ባለራዕይ ሕዝብ የማይነጥፍባት፣ በዓለም አደባባይ ገዝፋ የምትታወቀውና ባለደማቅ ታሪኳ ኢትዮጵያ የእልህ ግብግቡን ከዓባይ ጋር ገጠመች።
የዓባይን የግዞት ዘመን ለማክተም የዚህ ዘመን ትውልድም ቆርጦ ተነሳ። መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ፊሽካውም ተነፍቶ ከዓባይ ጋር ግጥሚያው ተጀመረ። የማይደፈረው ዓባይ ተደፈረ።
መላው ኢትዮጵያውያን ተረባረቡ። እልፍ አእላፍት ኢትዮጵያውያን ጉልበታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጊዜአቸውን፣ እውቀታቸውን ሳይሰስቱ፣ ለዓባይ ግድብ ለገሱ፤ ዓለም ተደነቀ። ብሔራዊ አንድነት በዓባይ ተገለጠ።
ከዓባይ ጋር የነበረው ግብግብ ከ14 ዓመታት በኋል በትውልድ ቅብብሎሽ በብርቱ የኢትዮጵያ ልጆች አሸናፊነት ተጠናቀቀ። ዓባይም ለሀገሩ እጅ ሰጠ። የግድቡ መጠናቀቅ ተበሰረ። ዓባይ ተገድቦ ጉልበትም፣ መብራትም፣ እራትም፣ ኩራትም ለመኾን በቅቷል።
“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” የሚባለውን ብሂል ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ አብረው በዓባይ ላይ እውን አደረጉት።
ዛሬ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በጉባ ሰማይ ስር ከፍ ብሎ ገዝፎ ታይቷል። የታሪካችን ከፍታ፣ የኀይላችን ሚዛን፣ የብርታታችን ምንጭ፣ የጽናታች ተምሳሌት፣ የአንድነታችን ማሠሪያ ገመድ፣ የብሔራዊ ቃልኪዳናችን ኾኗል።
“ዓባይ…ዓባይ
የሀገር ለምለም የሀገር ሲሳይ” ሲባል የነበረው ብሂልም እውን ኾኖ ዓባይ ለሀገር ልማት ውሎ ለኢትዮጵያ ሲሳይ ኾኗል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በዓባይ ላይ እውን ለማድረግ በፈጀው ዓመታት ብርቱ መሥዋትነት እየከፈሉ ለዚህ ካበቁት የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል የጸጥታ አካላት ተጠቃሽ ናቸው።
የአማራ ክልል ፖሊስ አባል ኮማንደር ታዬ ኃብተጊዮርጊስ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጀምሮ ለዚህ እስከሚደርስ ድረስ የጸጥታ አካላት በርካታ መስዋዕትነት መክፈላቸውን ተናግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሀገር ነው ያሉት ኮማንደር ታዬ የጸጥታ ኀይሉ ከሀገር ባልተናነሰ ስሜት ሲጠብቀው የኖረ መኾኑን አንስተዋል።
ግድቡ በዚህ ዘመን ተጠናቅቆ ለምረቃ በመብቃቱ እጅግ ደስተኛ መኾናቸውን ነው የገለጹት። ታላቁ የህዳሴ ግድብ የህልውናችን ጉዳይ ነው ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ የአይበገሬነት ተምሳሌት፣ እንደምንችል ሠርተን ያሳየንበት፣ የተከባሪነት እና የሀገራችንን ተጽዕኖ ፈጣሪነትን አጉልቶ ያሳየ ነው ብለዋል።
ሌላኛዋ የአማራ ክልል ፖሊስ አባል ኮማንደር አየሁ ታደሰ ግድቡ የመላው የጸጥታ አካላት አሻራ ያረፈበት መኾኑን ይናገራሉ። የጸጥታ አባላት በዱር በገደሉ እየተዋደቁ በመሥዋዕትነት እየጠበቁ ግድቡ ለምረቃ እንዲበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ነው ያነሱት።
የጸጥታ ኀይሉ እንደ ዐይን ብሌን ሲጠብቁት የኖረ ፕሮጀክት በመኾኑ ለምረቃ በቅቶ በማየታቸው የተለየ ደስታ እንደፈጠረላቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ለቀጣይም ለበለጠ ብርታት፣ ለተጨማሪ ግዳጅ እና ልማት የሚያነሳሳ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን