
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጳጉሜን 4 “የማንሠራራት ቀን” በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ነው።
በሥነ ሥርዓቱ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴን (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በማንሠራራት ቀን ተቋማት ሥራዎቻቸውን ለእይታ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዳንኤል ደሳለኝ የአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት እምርታን የሚያሳዩ ሥራዎችን መሥራቱን ተናግረዋል። በክልሉ ታላላቅ ለውጦች መመዝገባቸውንም ገልጸዋል።
የማንሠራራት ቀን ስናከብር የክልሉን የ25 ዓመታት የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት እቅድን በጋራ ለመተግበር ቃል የምንገባበት መኾን አለበት ብለዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የዛሬው ቀን እስካሁን ስናከብራቸው ከነበሩ የበዓል ዋዜማዎች ሁሉ የተለየ ቀን ነው ብለዋል።
ለዚህም ነው የማንሠራራት ቀን የተባለው ያሉት ኀላፊው ዛሬ ኢትዮጵያን አንገቷን ቀና ያደረገው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በሚመረቅበት ቀን የምናከብረው ቀን ስለኾነ ድርብ ስሜት አለው ነው ያሉት።
ይህ ቀን ለኢትዮጵያ የትንሣኤ ቀን ነው፤ ለጎረቤቶቿ ተስፋ መኾኗን ያሳየችበት፤ የኃይል አቅርቦቷን የጨመረችበት ነው ብለዋል። የሕዳሴ ግድብ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይዞ እንደሚመጣም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በግብርና እና በኢንዱስትሪ ዘርፍ እያስመዘገበችው ያለው ውጤት እውነትም የማንሠራራት ዘመን ላይ መኾኗን ማሳያ ናቸው ብለዋል። በማዕድን እና በሌሎች ዘርፎችም ታላቅ ለውጥ እየተመዘገበ መኾነው ነው የተናገሩት።
ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ እየተገነባ ያለውን የባሕር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ የማስፋፊያ ግንባታን መጎብኘታቸውንም ገልጸዋል። በክልሉ እየለሙ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ክልሉን በኢኮኖሚ ከፍ የሚያደርጉ መኾናቸውን ተናግረዋል። የማይቋረጥ የእድገት እንቅስቃሴ እንዲቀጥል ሁሉም መሪዎች በትኩረት እንዲሠሩም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን