
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ኾይ ከመሪዎችሽ እምባ የተረዳነው ሃቅ ቢኖር ከሰማነው እና ከምናውቀው በላይ ግፍ እና መገፋትን፤ እልክ እና ቁጭትን ታቅፈሽ ማሳለፍሽን ብቻ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ኾይ አንች ግን ማነሽ? ሕዝብሽ ከጥንት እስካሁን በፈተና ውስጥ አብዝቶ ይመላለስ ዘንድ የተፈረደበት፤ ስምሽ ሲጠራ፤ ገድልሽ ሲወራ በቅርብም በሩቅም ያሉ ሁሉ በዐይን ጥቅሻ ተሠባሥበው ጣቶቻቸውን የሚቀስሩብሽ፤ ከንፈሮቻቸውን የሚነክሱብሽ ለምን ይኾን? እናት ሀገር ኢትዮጵያ ኾይ የአንች በደል እና ገድል የቀሪውን ዓለም ሕዝብ እጁን አፉ ላይ ጭኖ ይገረምብሽ ዘንድ ግድ ያለሽ አንቺ ግን ከወዴት ነሽ? መዳረሻሽስ እስከወዲየት ይኾን?
ኢትዮጵያ ኾይ ግን ለምን ይኾን ነገስታቶችሽ እና መሪሽ ከጥንት እስከ ትናንት ለክብርሽ ሲሉ ሕይዎት እየገበሩ፣ በላብ እየተጠመቁ፣ በእምባ ዘለላ እየራሱ ለክብርሽ ከፊት፤ ለፍቅርሽ መስዋዕት መኾንን የታደሉ? እንደ ፈተናዎችሽ ብዛት፤ እንደፈታኞችሽ ብርታት እስከ ዛሬ ድረስ ህልውናሽ እንዴትስ አልጠፋ አላቸው?
እንደ ዓባይ ወንዝ በረዘመው ጥንታዊነትሽ፣ እንደ ራስ ደጀን በገዘፈው ታሪክሽ፣ እንደ ዳሎል የእሳት ፀዳል በተቀዳጀው መልክሽ፣ እንደ ምድር አሽዋ በበዛው ገድልሽ፣ እንደ ሰማይ ከዋክብትም በሚማርከው ኅብረ ብሔራዊነትሽ የተማረኩብሽ ሁሉ ሊማርኩሽ ብዙ ጣሩ፡፡
ዳሩ አንች የዘዎትር ሙሽራ ነሽ ሚዜዎችሽ ብርቱ፤ አጋፋሪዎችሽም የማይዝሉ ናቸውና ከቶም የማንም መኾን አልቻልሽም፡፡
ኢትዮጵያ ሆይ ለምን ይኾን የዓለም ፍትሕ ዓደባባይ ከድሮ እስከ ዘንድሮ በአንች ዘንድ ሚዛኑ የሚዛነፍ? እናት ሀገር ኢትዮጵያ ኾይ ከቶ ለምን ይኾን እጆችሽ አመድ አፋሽ የኾኑት? ደግሞስ ማህጸንሽ ለምለም፤ የአብራክሽ ክፋይ ብርቱ የማይነጥፍበት የኾነልሽ እንደምን ያለ ከርቤ ብትታጠኝ፤ እንዴትስ ያለ ሜሮን ብትቀቢ ነው?
ኢትዮጵያ ኾይ “ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብርም ዥንጉርጉርነቱን መቀየር ይቻለዋልን?” ተብሎ እንደተጻፈልሽ ኾነሽ ለመገኘት ዘመን በተቆጠረብሽ፤ በደል በተሰፈረብሽ ልክ ሁሉ እንደምን ህያው ኾኖ የመቀጠልን ብርታት ታደልሽ? ያንችስ “ለሰሚው ግራ ነው” ይሉት አይነት ብሂል ነው።
መበደልሽን ሁሉ ለቆጠረ እና መገፋትሽን ሁሉ ላስተዋለ የልብ ስብራቱ ጥልቅ ቢኾንም ሚስጥርሽን ላመሰጠረ እና ጽናትሽን ልብ ላለ ግን እውነትም የተስፋ ምድር ነሽ፡፡
መልካ ምድራዊ ዙሪያሽ ምድርን ሁሉ ያረሰርስ ዘንድ አፍላጋት ከማኅፀንሽ የሚፈስሱበት ፀጋን የታደለ ምድር ቢኾንም በተሰጠሽ ልክ እንዳትጠቀሚ የተጉ እና የበረቱ ብዙ አሜካላዎችም በዙሪያሽ ነበሩብሽ፡፡
የሕዝቦችሽ የዳቦ ጥያቄ እንዲዳፈን፤ የመሪሽ የማንሰራራት ራዕይ እንዲመክን ድካም ያልተሰማቸው ሴረኞች ዛሬም ድረስ አሉ፡፡
እማ ዛሬ ግን የትንሣኤሽ ቀን ከመቼውም ጊዜ በላይ ቅርብ የኾነ ይመስለናል፡፡ ይህ እምባ የራሄል እምባ ነው፤ የፈርኦንን ግፍ ያመላከተ፡፡ ይህ እምባ ባርነትን እና ተረጂነትን ተሻግሮ ወደ ነጻዋ እና የተስፋዋ ምድር የሚያደርስ እምባ ነው፡፡
ይህ እምባ የበዛ ቁጭት እና የዘመናት ብስጭት ገንፍሎ ያፈሰሰው የተስፋ ምልክት ነው፡፡ በዚህ እምባ የትናንቷ ኢትዮጵያ ውጣ ውረድ ታጥቦ የነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ የታየበት ነው፡፡
በዚህ እምባ አያሌ ክፋት ብርቱ መጓተት፤ እልህ አስጨራሽ ትግል እና አንፀባራቂ ድል ጎልተው ታይተዋል፡፡
ከዚህ ድል እና ስኬት ጀርባ ከፀጥታው ምክር ቤት እስከ አፍሪካ ኅብረት፤ ከሀያላን ሀገራት እስከ ቅርብ ጎረቤት በበጎም በክፉም የትናንቷ ኢትዮጵያ ብዙዎችን ታዝባለች፡፡ ነገ ግን እንደ ትናንቱ እንደማይኾን ልጆችሽ ፍፁም እርግጠኞች ነን፡፡
ኢትዮጵያ ኾይ ከመሪሽ እምባ የተረዳነው ሃቅ ቢኖር ከሰማነው እና ከምናውቀው በላይ ግፍ እና መገፋትን፤ እልህ እና ቁጭትን ታቅፈሽ ማሳለፍሽን ብቻ ነበር፡፡ እናም በዚህ እምባ፡-
“አታልቅስ ይሉኛል ላልቅስ እንጅ አምርሬ
ዕዳ በበዛባት፤ ፈተና ባፀናት ሀገር ተፈጥሬ” እንል ዘንድ ወድደናል፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!