የሕዳሴ ግድባችን የዓሣ ምርታችንም ምንጭ ነው።

8
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ትውልድ እና እድገቱ የፍቅር እና የብዝኀነት መገለጫ ከኾነው ደቡብ ነው። ኢትዮጵያዊነት ማንን ይመስላል ቢባል ደቡብን ከሚባልላቸው የብዝኀነት፣ የፍቅር እና የተስፋ ምድር ደቡብ ኢትዮጵያ ያደገው ኤርሚያስ ምኖታ የልቡን መሻት ይፈጽም ዘንድ በ2005 ዓ.ም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሠራተኛነት ወደ ቤንሻንጉል ክልል ጉባ አቀና።
ዛሬ ላይ ክንዴ ፊሽ የሚል ስም በመያዝ የሕዳሴ ግድብ ምርት የኾነውን ዓሣ በቲክቶክ የሚያስተዋውቀው ኤርሚያስ ምኖታ ተወልዶ ያደገው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ነው። ከ2005 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሠራተኛ ኾኖ አገልግሏል።
የጎዳና ተዳዳሪዎች ሠልጥነን በሕዳሴው ግድብ ሥራ ላይ እንድንሰማራ ተደረግን ሲልም የሕዳሴው ግድብ ሠራተኛ የኾነበትን ምክንያት ያስታውሳል።
በወቅቱ ስለ ሕዳሴ ግድብ ከነበረው ሀገራዊ መነሳሳት ጋርም በተያያዘ የግድቡ ሠራተኛ በመኾኑ ትልቅ ደስታ እንደተሰማው ገልጿል። በግንባታው መሳተፌ ብቻ ሳይኾን ሲጠናቀቅም በማየቴ ባለ ታሪክ ነኝ ብሏል። በሕይወቱ አንድ ለውጥ እና ተስፋ እንደሰነቀበት ነው ኤርሚያስ የገለጸው።
በግድቡ ሥራ ስንሳተፍ የበረሃውን ሙቀት፣ የሥራ ውጥረቱን፣ የዘመድ ናፍቆቱን… ሁሉ ችለን ግንባታው ተጠናቆ የሕዝቡን ደስታ ለማየት በጉጉት ነበር የምንናፍቀው በማለት ገልጿል።
በየቦታው ያለው ዘመድ ወዳጃችን ‘ግድቡ እየተሠራ ነው ወይ?’ በማለት አጥብቆ ይጠይቀን ነበር ያለው ኤርሚያስ ሕዝቡ ለግድቡ ካለው ጉጉት የተነሳም ስለ ሂደቱ የምንነግረውን ለማመን ይቸገር ነበር ብሏል።
ኤርሚያስ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በየጊዜው ያጋጠሙትን ችግሮች አልፎ ለፍጻሜ በመብቃቱ ፈጣሪውን እያመሰገነ ነው።
በ2015 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ከሕዳሴ ግድብ ሠራተኛነት የወጣው ኤርሚያስ አሁን ላይ ከግድቡ በታች በሚገኘው የውኃው ክፍል ዓሣ በማጥመድ እየተዳደረ ነው።
ከግድቡ በታች ባለው ውኃ የሚመረተው ዓሣ የሕይወት መሠረቱ ኾኗል። ከግድቡ ውጪ በገመድ መንጠቆ በሚያዝ ዓሣ ሕይወቱን እያሥተዳደረ መኾኑን የገለጸው ኤርሚያስ እንደየቀኑ ቢለያይም በሺዎች የሚቆጠር ብር እንደሚሠራ ነው የገለጸው። ዓሣውንም ከአምራቾች እየተቀበሉ ወደ ከተሞች የሚልኩ የተደራጁ ነጋዴዎች መኖራቸውንም ገልጿል።
ከግድቡ ላይ በዘመናዊ መልኩ ዓሣ ሲጠመድ የሚገኘው ምርት ከፍተኛ እንደሚኾን ነው የገለጸው። ለወጣቶችም ከፍተኛ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ያምናል።
የግድቡ ስፋት እና የሚሠራበት የዓሣ ልማት ተደማምሮ በሐይቁ ከፍተኛ የዓሣ ምርት እንደሚመረት ኤርሚያስ ያምናል። ይህም የኢትዮጵያን ተዝቆ የማያልቅ ሀብት ያመላክታል ብሏል።
ዋናው ሀሳቡ የሕዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ እንደነበር የገለጸው ኤርሚያስ በቀጣይ ከግድቡ ዓሣ ለማጥመድ የሚችልበትን ሕጋዊ መንገድ ለመጠየቅ እያሰበ መኾኑን ተናግሯል።
ኢትዮጵያውያን በቀጣይም ሌላ ታላቅ ፕሮጀክትን ቢጀምሩ ከፈጣሪ ጋር እንደሚሳካ ኤርሚያስ ያምናል። ዘመኑ የኛ የኢትዮጵያውያን የተስፋ እና የስኬት ዘመን ነው፤ የሰው ልጅ አዕምሮውን ሰላም እስካደረገው ድረስ በሥራ የማይሳካ ነገር የለም፤ የሕዳሴ ግድብ በጥልፍልፍ ዘመን አልፎ ለስኬት ከደረሰ ሌላው ቀላል ነው ሲልም ተስፋውን ገልጿል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleከተባበርን በርካታ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ልማቶችን መሥራት እንችላለን።
Next articleየአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የባሕርዳር አውሮፕላን ማረፊያ አዲስ የማስፋፊያ ግንባታን ጎበኙ።