
ሰቆጣ: ጳጉሜን 4/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአሸናፊነት ወኔ እና በኢትዮጵያዊ ጀግንነት ታጅቦ ለፍጻሜ ደርሷል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን ተከትሎ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎችም ሃሳባቸውን አካፍለዋል።
ክስተቱን ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከተባበርን በርካታ እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ የልማት ሥራዎችን መሥራት የሚያስችል አቅም እንዳለን ያየንበት ነው ብለውታል።
የአትክልት እና ፍራፍሬ ነጋዴው አቶ ሃብቱ ይስሃቅ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከሚሠሩት የንግድ ሥራ ያጠራቀሙትን ገንዘብ እንደደገፉ ያስታውሳሉ።
በልጆቻቸውም ስም ቦንድ ገዝተው አሻራቸውን እንዳስቀመጡ የገለጹት አቶ ሃብቱ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በመጠናቀቁ ደስታቸው ወደር እንደሌለው ነው ያብራሩት።
በወንዶች ጸጉር ቤት ሥራ የተሰማራው ወጣት ሰፊው ወልደስላሴ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጀመር ተማሪ እንደነበረ አስታውሶ ለእስክብሪቶ እና ለሻይ ከተሰጠው አብቃቅቶ ቦንድ እንደገዛ ያስታውሳል።
የሕዳሴው ዋንጫ ወደ ሰቆጣ ሲገባም ደም ከመለገስ ጀምሮ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረከተው ወጣት ሰፊው በይቻላል ወኔ የተጀመረው ግድብ ተጠናቅቆ በማየቱ ታላቅ ኩራት እንደተሰማው ገልጿል።
“እኛ ኢትዮጵያውያን የሚያምርብን በአንድነት ስንቆም ነው” ያሉት ደግሞ ሌላዋ የሰቆጣ ነዋሪ ወይዘሮ አለሚቱ ደሴ ናቸው።
በተለያየ ጊዜ ቦንድ እንደገዙ የሚናገሩት ወይዘሮ አለሚቱ ደሴ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሌላኛው የዓድዋ ድል ነው ብለውታል።
“ዛሬም ከገባንበት መለያየት ከወጣን ይህንን መሰል ድል ማስመዝገብ እንችላለን” ሲሉም አክለዋል።
ነዋሪዎቹ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ሌት ተቀን ለሠሩ ሠራተኞች፣ መሪዎች እና ለመላው ኢትዮጵያውያን የአንድነት እና የአሸናፊነት ማሳያ ለኾነው ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ የምረቃ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ ፦ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን