
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በታላቋ ኢትዮጵያ ልጆች ጥሪት፣ ላብ፣ ዕውቀት እና ደም የተገነባ የመቻል ትዕምርት ነው፡፡ ከእንግዲህ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንጅ ተመልካች አይደለችም፤ በአፍሪካ የታላቁ ግድብ ባለቤት እንጅ የረዥሙ ወንዝ ባለቤት የጥቅሙ ግን ተመልካች አይደለችም፡፡
የዓለማችንን ረዥሙንና በፈታኝ መልክአ ምድር ውስጥ የሚያልፈ ወንዝ ተባብረዉ የገሩ ኢትዮጵያውያን ሕልማቸዉን ከማሳካት የሚያስቆማቸዉ አንዳች ምድራዊ ኃይል አልነበረም፤ አይኖርምም፡፡
ሕዳሴ የኢትዮጵያ የተሰናሰነ ብዝኃነት ዐቅም የታየበት፣ በየክፍለ ዘመኑ የዓለምን ታሪክና ፖለቲካ የሚቀይር ተምሳሌታዊ ጥረትና ድል ከኢትዮጵያ እንደሚመነጭ ያስመሰከረ ነው፡፡ በ19ኛዉ ክፍለ ዘመን መገባደጃ በውስብስ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች አልፈዉ የዓድዋ ድልን ለዓለም የነፃነት ትግል ያበሩት ኢትዮጵያውያን ነበሩ።
ያ ድል የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግልን “ከዓድዋ ድል በፊት እና በኋላ” ብሎ የከፈለ ትልቅ የታሪክ አንጓ ነው፡፡
እነሆ በ21ኛዉ ዘመንም ኢትዮጵያውን ዳግማዊ ዓድዋን አሳክተዋል፡፡ የውኃ ፍትሐዊ አጠቃቀምን “ከኅዳሴ ግድብ በፊት እና በኋላ፣ የአፍሪካ ፖለቲካ ከኅዳሴ ግድብ በፊት እና በኋላ፣ ዓለማቀፍ ዲፕሎማሲ ከኅዳሴ ግድብ በፊት እና በኋላ” ብሎ መክፈል የሚችል ታላቅ ድል ተመዝግቧል፡፡
ይህ ድል ደግሞ የመላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ነው፡፡
ሕዳሴ የአይችሉም ትርክትን ‘ኢትዮጵያውያን ይችላሉ’ ወደሚል ትርክት ቀይሯል፡፡ከእኛው ውስጥ በተገዙ ተላላኪዎች የተፈጠሩ የእርስ በርስ ግጭት እና ዓለማቀፍ የዲፕሎማሲ ጫና፣ የማናውቃቸዉ የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች እና የታሪካዊ ጠላቶች ወጥመድ ተባብረዉ ያላስቀሩት ታላቅ ድል ነው፤ ሕዳሴ፡፡
ሕዳሴ የኢትዮጵያን የመልማት ዐቅም እና የአፍሪካዊያን ራስን የመቻል ብስራትና የእርስ በርስ ትስስር በእጅጉ የሚወስን ነው፡፡ሕዳሴ ታዳሽ ኃይል በማመንጨት በካይ የኃይል ምንጮችን የሚያስቀር ዓለም ሊደግፈዉ ሲገባ ሲፈትነዉ የኖረ፣ ግን በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት የተሳካ ልዩ ፕሮጀክታችን ነው፡፡
ሕዳሴ ለኢትዮጵውያን ከመኩሪያ ስኬት ባሻገር የኃይል ምንጭ፣ የዓሣ ሀብት መገኛ፣ የቱሪዝም መዳረሻም ጭምር ነው፡፡ሕዳሴ ለሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ምሳሌ ነው፡፡
ሕዳሴ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ከጎርፍ ተከላካይ ዋስትናቸው፤ በትነት ይባክን የነበረዉን ውኃ ማቆያቸው፤ ዓመቱን ሙሉ የተመጠነ ውኃ ማግኛቸው፤ ግድቦቻቸዉ በደለል እንዳይሞሉ መከላከያቸው ነው፡፡
እንዲህ ያለ ፋይዳ ያለዉን ግድብ መደገፍ የተገባ ነበር፤ ነገር ግን ይህንን ኹሉ ጥቅማቸዉን በመዘንጋት እና ሕዝባቸዉ በተሳሳተ መንገድ እንዲረዳው በማድረግ ታሪካዊ ጠላቶቻችን የኛን ተጠቃሚነት ለማደናቀፍ ሲጥሩ ኖሩ፡፡ግን አዘገዩን አንጅ አላስቀሩንም፡፡
እኛ ትዮጵያውያን የሰብአዊነትና የሞራል ባለቤት ሕዝቦች ነን፡፡ አይደለም ተፈጥሮ ለጋራ የሰጠንን ወንዝ ለብቻ በመጠቀም ሌሎችን ልንጎዳ፤ ባሕር ተሻግሮ ሊያጠፋን የመጣ ጠላትን አንዳች ዓለማቀፋዊ ሰብአዊ መብቶች ሕግ፣ ድርጅት እና አሠራር ባልነበረበት ማርከን፣ ተንከባክበን የያዝን፣ በክብርም ወደሀገሩ የመለስን የሰብአዊነትና የሞራል ባለቤቶች ነን፡፡
የታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ሕዝቦች እንዲያውቁልን የምንፈልገውም ይህንኑ ነው፡፡ ይሁን እንጅ በኃይል ከብልጽግና ጉዟችን ሊያደናቅፈን የሚቃጣን፣ ሉዓላዊነታችንን እና ነፃነታችንን ሊገዳደር፣ በተፈጥሯዊና ታሪካዊ ሀብታችን እንዳንጠቀም ሊከለክለን የሚችል ምድራዊ ኃይል አይኖርም፡፡
ኅዳሴ ለዚህ ማሳያ ትዕምርታችን ነው፡፡
በጋራ ችለናል፤ እንችላለንም!
ጳጉምን 3/2017 ዓ/ም
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት