የተማሪዎች ምዝገባ ተጠናክሮ መቀጠሉን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገለጸ።

4
ሰቆጣ: ጳጉሜን 3/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ነው። በሁሉም የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደርም ተጠናክሮ ቀጥሏል።
አሁን ላይ ሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ተማሪዎችን እየመዘገቡ ይገኛሉ።
በመድኃኒዓለም አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪዎቹ አፀደ ወንድሙ እና አፀደ ጸጋዬ ቀድመው በመመዝገባቸው ለትምህርት የሚያሥፈልጉ ግብዓቶችን እንዲያሟሉ አግዟቸዋል።
ትምህርት ቤቱም ቀድመው ለተመዘገቡ ተማሪዎች ሙሉ የመማሪያ መጽሐፍትን ከምዝገባ ጎንለጎን መስጠቱ ለተማሪዎች መነሳሳትን የሚፈጥር ነው ብለዋል ተማሪዎቹ።
ልጆቻቸውን ሲያስመዘግቡ አሚኮ ያገኛቸው አቶ አዳነ ታፈረ ልጃቸውን መከታተል እና መደገፍ የሚጀምሩት ከምዝገባው ጀምሮ እንደኾነ ጠቁመዋል።
አቶ አዳነ ወላጆች የምዝገባ ጊዜው ሳይዘጋ እንደሳቸው ሁሉ ልጆቻቸውን ማስመዝገብ እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት።
የመድኃኒዓለም አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ኃይለሚካኤል ወንድአጥር በ2018 የትምህርት ዘመን ከ1ሺህ 700 በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ አቅደው እስካሁን ከ700 በላይ ተማሪዎችን መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
ምዝገባው ተጠናክሮ መቀጠሉን የተናገሩት ርእሰ መምህሩ ወላጆች ልጆቻቸውን ቀድመው በማስመዝገብ ለትምህርት ጥራት መጠበቅ ኀላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።
በሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ሦስት የግል እና 11 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ሲኾን በእነዚህም የተማሪ ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝ የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ አማረ ወልደገብርኤል ገልጸዋል።
በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ6 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች የተመዘገቡ ሲኾን በዚህም የዕቅዳቸውን 73 ነጥብ 2 በመቶ እንዳሳኩ ጠቅሰዋል።
ምክትል ኀላፊው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ2 ሺህ 300 በላይ ተማሪዎችን በመመዝገብ የእቅዳቸውን 55 ነጥብ 2 በመቶ መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የተማሪ ምዝገባው በተጠናከረ መንገድ መቀጠሉን የነገሩን ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ፍታለሽ ምህረቴ ናቸው።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በአጠቃላይ ከ263ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ አቅደው እስከ ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም ድረስ ከ148ሺህ በላይ ተማሪዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
የ2018 የትምህርት ዘመን መስከረም 05/2018 ዓ.ም እንደሚጀምር የጠቆሙት ወይዘሮ ፍታለሽ ለዚህም አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ በማጠናቀቅ የተማሪ ምዝገባው ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ እንደኾነ ነው የገለጹት።
የተማሪ ወላጆች እና ተማሪዎች ቀድመው በመመዝገብ ለአዲሱ የትምህርት ዘመን እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከአየር ንብረት እርዳታ ወደ አየር ንብረት ኢንቨስትመንት ለውጥ ሊደረግ እንደሚገባ አሳሰቡ።
Next articleየታሪክና ፖለቲካ ብያኔን የለወጥንበት የጋራ ችሎታችን ትዕምርት ነው!