የእንግጫ ነቀላ እና የከሴ አጨዳ በዓል የቱሪዝም መዳረሻ እንዲኾን እየተሠራ ነው።

4

ደብረማርቆስ: ጳጉሜን 3/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን የእንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ በዓል ማጠቃለያ ዝግጅት በደብረ ማርቆስ ከተማ ተካሂዷል። የክረምቱ ወቅት መገባደድን እና የአዲስ ዓመት መቃረብን ከሚያበስሩ ባሕላዊ ክዋኔዎች መካከል አንዱ የኾነው የእንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ በዓል በምሥራቅ ጎጃም ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ሲከበር ቆይቷል።

 

በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች ሲካሄድ የቆየው የእንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ በዓል እንደ ዞን የማጠቃለያ ዝግጅት በደብረ ማርቆስ ከተማ ተካሂዷል፡፡

 

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ሙሉ ዓለማየሁ የእንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ በዓል በዞኑ ማኅበረሰብ ዘንድ ረጂም ዘመናት ያስቆጠረ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

 

በዓሉ በአደባባይ እንዲከበር መደረጉ ለቀጣይ ባሕል እና ትውፊቱን ለትውልድ ለማስተላለፍ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

 

የዞኑ ማኅበረሰብ የማንነት መገለጫ የኾነው የእንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ በዓል የቱሪዝም መዳረሻ እንዲኾን የባሕሉ ባለቤቶች እና አጋር አካላት የሚጠቅባቸውን ድርሻ ማበርከት አለባቸው ነው ያሉት።

 

በማጠቃለያ ዝግጂቱ ላይ የተገኙት የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳደር ተወካይ ኅላፊ ባንተላይ ደምሰው ለእንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ በዓል ትኩረት በመስጠት ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

 

ከየወረዳዎቹ የመጡ የበዓሉ ታዳሚዎች የእንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ የነፃነት እና አንድነት በዓል ከመኾን ባለፈ የቀደምት አያቶችን ታሪክ እና ወግ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍበት መኾኑን ተናግረዋል።

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየኢትዮጵያ ምድር ማጌጫ አደይ አበባ።
Next articleየውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት 113 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል።