የኢትዮጵያ ምድር ማጌጫ አደይ አበባ።

13

አዲስ አበባ: ጳጉሜን 3/2017 ዓ.ም (አሚኮ) መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ

እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዕዳ።

 

ከያኒያን ይህችን የግጥም ስንኝ ደርሰው በዜማ አሽተው ለአድማጩ ሲያደርሱ በአዲስ ዓመት ዘመድ ከዘመዱ፤ ጓደኛ ከጓደኛ እንኳን አደረሰን አደረሳችሁ የሚባባልበት መኾኑን ለማሳየት በማሰብ ነው።

 

አሮጌውን ዓመት ሽረን አዲሱን ዓመት ስንቀበል ታዲያ ጋራ ሸንተረሩ የተስፋ፣ የሰላም እና የብርሃን መገለጫ በኾነችው አደይ አበባ ይሞላል።

 

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሃብት አያያዝ ተመራማሪ እና አደይ አበባ ላይ ጥናት ያደረጉት በላይነህ አየለ (ዶ.ር) አደይ አበባ አስትራሼ (Asteraceae) የሚባል ቤተሰብ ዝርያ እንደኾነች እና በዓለም ላይም ከ230 በላይ ዝርያ እንዳላት ያስረዳሉ።

 

ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የምትበቅለው አደይ አበባ በሳይንሳዊ ስያሜዋ ባይደን ማክሮፔትራ (Bidens macroptera) እንደምትባልም ነግረውናል።

 

አደይ አበባ ከሌሎች ዝርያዎች የሚለያት አጭር የመኖር ዕድሜ ያላት መኾኑ እና በአንድ ወቅት ብቻ በቅላ ሂደቷን በአንድ ወቅት ጨርሳ የምትጠፋ መኾኗን ያስረዳሉ።

 

የአደይ አበባ የቆይታ ጊዜ በጣም አጭር ነው፤ ይህ ደግሞ የክረምት መገባደድን እና የበጋ መምጣትን በአበቦች ጫፍ ላይ በሚገኙ ሆርሞኖች የሚለዩበት ተፈጥሮ የታደሉ መኾናቸው የሚያሳይ እንደኾነ ተመራማሪው ያነሳሉ።

 

በአጭር ጊዜ ውስጥ ዑደታቸውን ጨርሰው አበባ ኾነው የሚጠፉት አደይ አበባወች “ከእኛ ኢትዮጵያውያን ጋር ደግሞ የዘመን መለወጥ ጋር በመቆራኘታቸው ሁሌም አደይ አበባን እንድናስታወስ አድርጎናል” ይላሉ ዶክተር በላይነህ አየለ።

 

አደይ አበባን ከፀሐይ ጋር የመሰሏት ተመራማሪው አደይ አበባ የተስፋ ምልክት ናት ይላሉ። ዶክተር በላይነህ አየለ አደይ አበባ በሌላው ዓለም ለተለያዩ አገልግሎቶች እንደምትውልም አንስተዋል።

 

በላቲን አሜሪካ ለሻይ፣ ለመድኃኒት እና ለስዕል ቀለም እንደሚጠቀሙባትም አብራርተዋል።

 

አደይ አበባ ለንቦች ምቹ ምግብ እንደኾነች የሚያነሱት ዶክተር በላይነህ አየለ የሥነምህዳሩን ሚዛን ለማስጠበቅም እንደሌሎች ፍጥረቶች ሁሉ አበርክቶ አላት ብለዋል።

 

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleከበዓል ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ ከሚችሉ ወንጀሎች እና አደጋዎች ራስን መጠበቅ ይገባል። 
Next articleየእንግጫ ነቀላ እና የከሴ አጨዳ በዓል የቱሪዝም መዳረሻ እንዲኾን እየተሠራ ነው።