ከበዓል ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ ከሚችሉ ወንጀሎች እና አደጋዎች ራስን መጠበቅ ይገባል። 

5

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ መጭውን የዘመን መለወጫ በዓል አስመልክቶ ለኅብረተሰቡ የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፏል።

 

በክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 

የ2018 የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም እንዲከበርም የጸጥታ ማስከበሪያ ዕቅድ በማዘጋጀት እና በሀሳብ በማዳበር ከላይ እስከ ታችኛው ዕርከን ወርዶ እየተሠራበት ይገኛል ብለዋል።

 

የዘመን መለወጫ በዓል ሲመጣ በሚፈጠረው መስተጋብር ምክንያት የሰዎች በስፋት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንደሚስተዋል መምሪያ ኃላፊው ተናግረዋል። ይሄንን ተከትሎ በሚፈጠር መጨናነቅ የትራንስፖርት ተገልጋዮች ከታሪፍ በላይ መክፈል የለባቸውም ብለዋል።

 

አስገዳጅ ነገር ሲያጋጥም ደግሞ ሁሉም የትራፊክ ፖሊሶች እና መሪዎች በየመስመሩ ስለሚቆጣጠሩ ኹኔታውን በመጠቆም ወንጀልን በጋራ መከላከል እንደሚገባም መልእክት አስተላልፈዋል።

 

የትራፊክ አደጋ በክልሉ አሳሳቢ ኾኗል ያሉት መምሪያ ኀላፊው በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ 1ሺህ 40 አደጋዎች መድረሳቸውን አስታውሰዋል። በዚህም የበርካታ ሰዎች ሕይዎት ጠፍቷል፤ አያሌ ንብረት ወድሟል። በበዓል ወቅት ደግሞ አደጋዎች እንደሚበዙ አስታውሰው አደጋን መቀነስ የሚቻለው ሁሉም ሕግን አክብሮ ሲያገለግል እና ሲገለገል ነው ብለዋል።

 

በበዓላት ወቅት ከፍተኛ ግብይት ይከናወናል፤ ገበያተኛው በተለያዩ መንገዶች እንዳይታለሉ እና እንዳይጭበረበሩ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

 

እንደ ሀገር እና ክልል ሀሰተኛ ገንዘብ በስፋት እንደሚዘዋወር የጠቆሙት ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ በጥሬ ገንዘብ ግብይት የሚከናወን ከኾነ ገንዘቡ ትክክለኛ ስለመኾኑ በጥንቃቄ ማረጋገጥ እንደሚገባ የጥንቃቄ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

በተለይ በሞባይል ስልክ ግብይት ሲፈጸም ገንዘብ ከማስተላለፍ በፊት ደጋግሞ ማረጋገጥ ግድ ይላል ነው ያሉት።

 

ማንኛውም የወንጀል ጥርጣሬ ሲኖርም በአቅራቢ ለሚገኙት የጸጥታ ኃይሎች መጠቆም እንደሚገባ ኃላፊው መክረዋል።

 

በአማራ ክልል በ2017 ዓ.ም 191 ሺህ 700 ሀሰተኛ ብር ሲዘዋወር በፖሊስ ጥብቅ ክትትል እና በማኀበረሰቡ ጥቆማ ተይዞ ምርመራውን በማጣራት ለሕግ መቅረቡን ነው ረዳት ኮሚሽነሩ ያስታወሱት።

 

ማኀበረሰቡ ለምግብነት የሚውሉ ልዩ ልዩ የግብዓት ዓይነቶችን ሲገዛም ከበዓድ ነገር የጸዳ መኾኑን አጣርቶ መኾን እንዳለበት ኀላፊው ጠቁመዋል።

 

በበዓላት ጊዜ ከሚኖረው ሰፊ የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ኅብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግም ረዳት ኮሚሽነሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

 

ማንኛውም የኀብረተሰብ ክፍል በማንኛው ዕለት እና ቀን ወዘ ልውጥ ሰው ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኙ የጸጥታ ኃይሎች ጥቆማ በመስጠት ሊደርስ የሚችለውን ወንጀል እና ጥፋት አስቀድሞ ለመቆጣጣር አጋዥ መኾን አለበት ሲሉም ተናግረዋል።

 

ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እመርታ ለዘላቂ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት በኮምቦልቻ ከተማ ጳጉሜን 3 በፓናል ውይይት እና ጉብኝት እየተከበረ ነው። 
Next articleየኢትዮጵያ ምድር ማጌጫ አደይ አበባ።