
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ ከባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ ጋር በመተባባር በሮቦቲክ ቴክኖሎጅ ልዩ ተሰጥኦ ላላቸው ተማሪዎች ሥልጠና እየሰጠ ነው።
በሥልጠናው ላይ ከባሕር ዳር ከተማ እና አካባቢው ካሉ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንጅነሪንግ እና ሒሳብ ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተር ዓለሙ ተስፋዬ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች መማሪያ የሚኾን ግብዓት ከማሟላት ጀምሮ ብቁ አሠልጣኝ መምህራንም በመመደብ ተማሪዎችን እያሠለጠነ መኾኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው አማካሪ በመመደብ ምቹ የመማሪያ አካባቢን መፍጠሩንም አንስተዋል። እየወሰዱት ያለው ሥልጠና ተማሪዎች በሮቦቲክ ቴክኖሎጅ ሠልጥነው ለገበያ በሚያቀርቡ የቴክኖሎጅ ምርቶች ለሽያጭ ደረጃ እንዲደርሱ መንገድ ማሳየት ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ የቢዝነስ ኢንኩቬሽንና ስታርት አፕ ድጋፍ ባለሙያ ሀብታሙ ስሜነህ ሥልጠናው የተለየ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች በሮቦቲክ ቴክኖሎጅ አቅማቸውን ለማሳደግ ያለመ ነው ተብለዋል። የፈጠራ ችሎታቸውን ከመሠረቱ ጀምሮ እንዲያዳብሩ የሚያስችል እንደኾነም ነው የገለጹት።
ሥልጠናው ለ247 ተማሪዎች በነጻ እየተሰጠ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት። እንደ ክልል እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት “በቴክኖሎጅ እና በፈጠራ ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ስለመኾኑም” አመላክተዋል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ ሥልጠናውን በማስፋት በሌሎችም አካባቢዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ከባሕር ዳር አካዳሚ እንደመጣ የነገረን ተማሪ ኢዩስያስ ስማቸው በክረምት ወቅት በቴክኖሎጅ ዘርፍ የሮቦቲክስ ሥልጠና እየሠለጠነ መኾኑን ገልጾልናል።
ሥልጠናው በቀጣይም በቴክኖሎጅ ዘርፍ ለመማር ጥሩ ግንዛቤ እያስገኘለት መኾኑን ነው የገለጸው። ባገኘው እውቀትም በተለያዩ ፕሮጀክቶች በመሳተፍ ለማኀበረሰቡ ችግር ፈች የኾኑ የቴክኖሎጅ ውጤቶችን ለማበልጸግ እንዳሰበ ነግሮናል።
ከሪስፒንስ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት የመጣችው ተማሪ ኤፍራታ ሃይማኖት እየወሰደችው ያለው ሥልጠና ከንድፈ ሃሳብ ባለፈ የተግባር ትምህርት እንድታገኝ ያስቻላት መኾኑንም ገልጻለች።
ከተለመደው የትምህርት አሰጣጥ ሂደት በተለየ መንገድ በተግባር መሰጠቱ የማይረሳ እና ሁሌም የሚዘልቅ እውቀት ለማግኘት እንደሚረዳ ነው የገለጸችው።
አንድን ነገር ስንሠራ ውጤት ጠብቀን ነው ያለችው ተማሪ ኤፍራታ በማዕከሉ የሚሰጡት ሥልጠናዎች ወደ ፊት የኀብረተሰቡን ችግሮች በቴክኖሎጅ ታግዞ ለማቃለል መሠረት የሚጥል እና ውጤት የሚያመጣ እንደኾነ ነው የተናገረችው።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!