
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በቀጣዮቹ 10 ዓመታት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ሽፋን እንዲኖረው በትኩረት እንደሚሠራ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታውቋል።
በክልሉ እየታዬ ያለው ከፍተኛ የኢንዱስትሪ አብዮት መልኩ በብዙ መንገድ የሚገለጥ እምርታ የታየበት ዘርፍ እየኾነ ነው ማለት ይቻላል።
ለዚህ ማሳያውም በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል በ2017 በጀት ዓመት የተሳካ ሥራ ከውነዋል ከተባሉት ክልሎች አንዱ የአማራ ክልል ኾኖ እውቅና መሰጠቱ ይታወሳል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በበጀት ዓመቱ 336 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 2 ሺህ 825 አዳዲስ የሀገር ውስጥ እና የውጭ አልሚዎች በክልሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ተመቻችቷል ብለዋል፡፡
88 አነስተኛ፣ 86 መካከለኛ አንዲሁም 19 ከፍተኛ በድምሩ 193 አምራች ኢንዱስትሪዎችን ወደ ምርት ማስገባት ተችሏል ነው ያሉት። 653 ሌሎች የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ምርት እና አገልግሎት ማስገባት እንደተቻለም ነው የገለጹት፡፡
ከ109 ሺህ ቶን በላይ የኢንዱስትሪ ምርት ወደ ውጭ በመላክ 152 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ተችሏል ብለዋል። 443 ሺህ ቶን የሚጠጋ ተኪ ምርት በማምረት 843 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ማዳን እንደተቻለም ገልጸዋል።
የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት በዓመቱ በኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት መርሐ ግብር 193 አምራች ኢንዱስትሪዎች በአዲስ መልክ ወደ ማምረት ሥራ ስለመግባታቸውም ተነስቷል።
የቢሮው ኀላፊ እንድሪስ አብዱ እነዚህ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ያሉ ናቸው ብለዋል። አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ወደ ምርት በመግባታቸው የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የራሱን አሻራ አሳርፏል ነው ያሉት።
ዘርፉ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ እና ክልላዊ የኢኮኖሚ ድርሻ እንዲወጣ ከኢንቨስትመንት መሳብ ጀምሮ ምርት ተመርቶ ለገበያ እስኪቀርብ ድረስ ባለው የእሴት ሰንሰለት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ መሥራትን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
ወደ ውጭ ከተላከው ምርት ባሻገር “843 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ግምት ያላቸውን ምርቶች በማምረት ሀገሪቷን ከተጨማሪ ጫና ማላቀቅ የተቻለበት ዓመት እንደነበር” ኀላፊው አንስተዋል።
እነዚህ አምራች ኢንዱስትሪዎች በጥቅሉ በአማራ ክልል 70 ሺህ ለሚጠጉ ወገኖች የሥራ ዕድል ስለመፍጠራቸውም ተናግረዋል። ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተመዘገበው የዘርፉ 10 ነጥብ 7 ዕድገት የአማራ ክልል አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ነው የገለጹት። በኢትዮጵያ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ሊያስወጡ የሚችሉ ተኪ ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት እንዲመረቱ አድርጓል ብለዋል።
በቀጣይ 10 ዓመታት የአማራ ክልልን ማክሮ ኢኮኖሚ ለመምራት የሚያስችል ስትራቴጂ ነድፎ ቢሮው ወደ ሥራ ገብቷል። ከአሁን በፊት ቦታ ወስደው በፍጥነት ወደ ልማት ባልገቡ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ ስለመወሰዱም የቢሮው መረጃ ያሳያል።
“በክልሉ 986 አልሚዎች ወደ ተግባር ባለመግባታቸው እርምጃ ተወስዶባቸዋል” ብለዋል ቢሮ ኀላፊው። በተገባደደው ዓመት የኢንዱስትሪን የማምረት አቅም 61 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ 59 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ ነው የተናገሩት።
አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮች ማለትም የፋይናንስ፣ የመሬት፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦት እና አገልግሎት አሰጣጥ በሚፈለገው ልክ ፈጣን እና ቀልጣፋ ባለመኾኑ ዘርፉ ባለው እምቅ አቅም ልክ ውጤታማ ነው ለማለት አያስደፍርም ብለዋል።
በአማራ ክልል ደረጃ የተቀረጸው የ25 ዓመታት የልማት እና እድገት አሻጋሪ ዕቅድ ለኢንዱስትሪው እና ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ትልቅ ትኩረት ስለመሰጠቱም አቶ እንድሪስ ተናግረዋል።
ይህ እቅድ በየአምስት ዓመቱ እየተመነዘረ ተግባራዊ የሚደረግ ሲኾን በቢሮ ደረጃ ተግባሩን በ2018 በጀት ዓመት በተጠና መንገድ ለማስኬድ ሥራው ተጀምሯል ነው ያሉት።
በ2018 በጀት ዓመት ማነቆዎችን መፍታት እና በአሻጋሪ የልማት እና የቁጭት ዕቅድ በተቀመጡ የትኩረት
መስኮች ለመሥራት ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ኤልያስ ፈጠነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!