ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ጳጉሜን 3 “እመርታ ለዘላቂ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት አክብሯል።
የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ እያደገ ለሚገኘው ኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ ማሟላት እና የውጭ ምንዛሬን የሚያስገኙ ምርቶችን ማምረት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት ለውጦችን ማስመዝገብ መቻሉን ነው የተናገሩት።
ክልሉ በ2017 የምርት ዘመን ምርትን በአማካይ በሄክታር ከ28 ኩንታል ወደ 32 ኩንታል ማሳደግ ተችሏል ብለዋል። በክልሉ አንዳንድ ወረዳዎች ላይ ተወስኖ የነበረውን የሩዝ ምርት ወደ ስምንት ዞኖች በማስፋት በዓመት 280 ሺህ ሄክታር ሩዝ ማልማት መቻሉንም ነው የገለጹት።
ለአረንጓዴ አሻራ፣ ለበጋ ስንዴ ልማት እና ለፍራፍሬ ልማት በተሠጠው ትኩረት ለውጥ መመዝገቡንም አንስተዋል።
ባለፈው ዓመት በቡና ልማት ብቻ 9 ሺህ ሄክታር መሬት፣ በዚህ ዓመት ደግሞ 12 ሺህ ሄክታር ቡና መሬት መሸፈን መቻሉን ገልጸዋል። በየዓመቱ ከ27 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ እና በመሳሰሉ የፍራፍሬ ልማት የተሸፈነ መኾኑንም በማሳያነት አንስተዋል።
የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ለሜካናይዜሽን ልማት በተሰጠው ትኩረት የትራክተር ቁጥር ወደ 2 ሺህ 100 ማድረስ ተችሏል ነው ያሉት ኀላፊው። 80 ኮምባይነሮችን ወደ ክልሉ ማስገባት እንደተቻለም ገልጸዋል።
በሌማት ትሩፋትም የዝርያ ማሻሻል፣ የመኖ ልማት፣ የእንቅላል እና የሥጋ ዶሮ እንዲሁም የወተት ምርት እያደገ መምጣቱን ነው የገለጹት።
በ2018 በጀት ዓመት የውጭ እርዳታን ለማስቀረት ግብ ተቀምጦ እየተሠራ መኾኑን ነው ዶክተር ድረስ የተናገሩት። “የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሉዓላዊነት ጉዳይ እንደኾነም” ገልጸዋል።
በ25 ዓመቱ አሻጋሪ ዕቅድ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ዓምስት ዓመታት ላይ ግብርና ዋነኛ ተዋናይ እንዲኾን ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!