
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 3/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ኃይሌ አበበ ባለፉት ዓመታት በክልሉ ለማዕድን ዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የግጭት ምንጭ ከመኾን ወጥቶ የምጣኔ ሃብት አማራጭ ሆኗል ብለዋል።
ክልሉ ካለው 185 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የቆዳ ስፋት ውስጥ 25 በመቶ በሚኾነው ቦታ ላይ 51 የማዕድን አይነቶችን በመለየት ወደ ውጤት የመቀየር ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የለሚ ስሚንቶ ፋብሪካ እንዱ ማሳያ መኾኑንም ገልጸዋል። በ2022 ዓ.ም በክልሉ ተጨማሪ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል።
የማርብል እና ግራናት ፋብሪካዎች በባሕርዳር፣ በቡሬ፣ በደብረ ማርቆስ እና በመሳሰሉ ከተሞች በግንባታ ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ በ2017 ዓ.ም 100ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ክልሉ ማዕድንን ወደ ውጭ በመላክ 10ሚሊዮን ዶላር፣ የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ደግሞ 113 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘት መቻሉን በማሳያነት አንስተዋል።
የማዕድን ሃብት የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት፣ የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት፣ የመንግሥትን ገቢ በማጠናከር፣ የቴክኖሎጅ እና የዕውቀት ሽግግር በማምጣት እና የሀገርን የኀይል ሚዛን በማስጠበቅ ካላቸው ሚና አኳያ በአሻጋሪ ዕቅዱ ትኩረት ከተሰጣቸው ተቋማት አንዱ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን