“የጀመርናቸውን በመጨረስ፣ ያለምናቸውንም በመጀመር የኢትዮጵያን እመርታ ለማብሰር እየሠራን ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

6
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የእመርታ ቀን “እመርታ ለዘላቂ ከፍታ” በሚል የሚከበረው ጳጉሜን ዐ3 በባሕር ዳር ከተማ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ነው።
በዕለቱ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እና ሌሎችም የከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች ከከተማው ውስጥ የሚከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል። ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ተከፋፍሏል፤ ለአቅመ ደካሞችም የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር ተከናውኗል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባስተላለፉት መልዕክት “የእመርታ ቀንን ስናከብር በከተማ አሥተዳደሩ የተጀመሩ ትልልቅ የልማት ሥራዎችን በማጠናቀቅ እና ለነዋሪዎቿ እንካችሁ በማለት ነው” ብለዋል።
ባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በርካታ ሰው ተኮር ልማቶችን እያከናወነች ነው፤ የከተማዋ መንገዶች እና አደባባዮች በጽዳትና ውበት እየደመቁ ነው፤ አቅመ ደካሞች ከመቸገር እንዲወጡ የሚያስችሉ ሥራዎችም እየተከናወኑ ነው ብለዋል ከንቲባው።
እኛ ኢትዮጵያውያን ስንተባበር እና በጋራ ስንቆም ለዓለምም ጭምር ተምሳሌት የሚኾን እመርታ እናስመዘግባለን፤ ለምርቃት ዝጎጁ የኾነው የህዳሴ ግድብ ለዚህ ተግባራዊ ምስክር ነው ብለዋል። አትችሉም ሲሉን ችለናል፣ አይጀምሩም ሲሉንም ጀምረን ጨርሰናል ነው ያሉት።
እስካሁን ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሃብቶችን በመፈለግ ወደ ጥቅም የማስገባት ሥራ እየተከናወነ ስለመኾኑ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል። ጎርጎራ በተፈጥሮው ድንቅ ቦታ ቢኾንም እስካሁን ድረስ በወጉ አለማም ነበር፤ አሁን ግን ውበቱን የሚገልጥ እና የሚመጥነውን ልማት አግኝቶ ሁነኛ የቱሪዝም ቦታ ለመኾን በቅቷል ነው ያሉት።
በባሕር ዳር ከተማ ዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይም አንዱ የእመርታችን ማሳያ ነው ያሉት ከንቲባው ድልድዩ ለአማራ ክልል ብቻ ሳይኾን ለመላ ኢትዮጵያውያን እና ለምስራቅ አፍሪካም ሁነኛ የመተሳሰሪያ መንገድ ነው ብለዋል።
በባሕር ዳር ከተማ ጣናን የመግለጥ፣ በኮሪደር ልማት የማስዋብ፣ አቅመ ደካሞችን እንደቤተሰብ የመንከባከብ እና የመደገፍ፣ ወደ ልማት ያልገቡ ቦታዎችን የማልማት እና የሕዝብ መናፈሻ ቦታዎችን የመገንባት ሥራ ሲከናወን ስለመቆየቱም ጠቅሰዋል።
የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት በውጤታማነት ተጠናቅቋል፤ ይህም ፕሮጀክትን በፍጥነትና በጥራት የመፈጸም ተልዕኮ የተሳካበት ነበር ብለዋል። በከተማዋ 30 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ሥራ በእቅድ ተይዞ እየተሠራ ስለመኾኑም ጠቁመዋል። በቀጣይም ከዓባይ እና ጣና ጋር ተያይዞ በልዩነት የሚከናወን የኮሪደር ልማት እንደሚጀመር እና ለባሕር ዳር ከተማ ልዩ ውበት በሚሰጥ መልኩ ተሠርቶ እንደሚጠናቀቅ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።
በከተማዋ ውስጥ 22 ኪሎ ሜትር ዘመናዊ የአስፋልት መንገድ ለመገንባት ታቅዶ በመከናወኑ አብዛኛውን መፈጸም ተችሏል፤ ባሕር ዳርን የውብ ጎዳናዎች ባለቤት የማድረግ ሥራም በተግባር ተከናውኗል ነው ያሉት።
የእምርታ ቀንን ስናከብር ተግባራዊ ሥራዎችን በማከናወን እና ሥኬቶችን በማስመዝገብ ጭምር መኾን እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል። ባሕር ዳር ከተማ ቱሪስቶች ለማየት የሚጓጉላት እንድትኾን እየተሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
“የጀመርናቸውን በመጨረስ፣ ያለምናቸውንም በመጀመር የኢትዮጵያን እመርታ ለማብሰር እየሠራን ነው” ነው ያሉት።
በአዲሱ ዓመት የተቸገሩትን በማገዝ፣ የትምህርት ቁሳቁስ ለተቸገሩ በመሙላት እና በመፈቃቀር መሻገር እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article“የአብሮነት መገለጫ የኾነው የሩፋኤል በዓል በዓባይ ወንዝ”
Next articleየጳጉሜን 3 የእመርታ ቀን በደሴ ከተማ በተለያዩ ኹነቶች ተከብሯል።