“የአብሮነት መገለጫ የኾነው የሩፋኤል በዓል በዓባይ ወንዝ”

3
ባሕር ዳር፡ ጳጉሜን 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጳጉሜን 3 ዓመታዊው የሩፋኤል መንፈሳዊ በዓል የሚከበርበት ቀን ነው፡፡
በዓሉ በሁሉም አካባቢ የሚከበር በዓል ቢኾንም እንኳ በደጀን እና ጎሃ ጽዮን መካከል በዓባይ ወንዝ ሁለቱ ጠርዞች ላይ የሚከበረው አከባበር ግን በድምቀቱ፣ በአከባበር ሥነ ሥርዓቱ እና በተሳታፊዎቹ ቁጥር ልዩ እንደኾነ ይነገርለታል።
በአማራ እና በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ከጥንት ጀምሮ የነበረው ይህ የጋራ ሃይማኖታዊ በዓል ጊዜ በማይሽረው፣ ማዕበል በማያናውጠው፣ ፍቅር እና ትስስር ዘንድሮም እየተከበረ እንደኾነ የደጀን ወረዳ የባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የሹምነሽ የኔውድ ተናግረዋል።
የሩፋኤል በዓል የአማራ ክልል እና የኦሮሞ ክልል አዋሳኝ ወረዳዎች በብዛት የሚገናኙበት፤ በታላቁ ዓባይ ወንዝ ዳር ተቀምጠው ዓመቱን እንዴት እንዳሳለፉ የሚወያዩበት፤ አዲሱን ዓመትም በተስፋ ለመጀመር በአንድነት እና በፍቅር በዓባይ ወንዝ የሚታጠቡበት እና የሚጠመቁበት በዓል እንደኾነ ኀላፊዋ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ቦታው በሚያቀኑ በርካታ እንግዶች ደምቆ ዓባይ ድልድይ አቅራቢያ በልዩ ሁኔታ የሚከበረው ይህ በዓል ከመቼ ጀምሮ እዛ ቦታ ላይ አሁን ባለበት ሁኔታ እንደሚከበር ለመግለጽ እንደሚያስቸግርም የሹምነሽ የኔውድ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸውልናል።
የሁለት ማኅበረሰቦችን አብሮነት የሚያጎላው ይህ የሩፋኤል ሃይማኖታዊ በዓል በዋናነት ጳጉሜን 3 እንደሚከበር የነገሩን ኀላፊዋ አሁን ላይ ባለው የሰላም ጉዳይ ግን የበዓሉ አከባበር እየተቀዛቀዘ እንደመጣ ጠቁመዋል።
ምንም እንኳ የሩፋኤል ሃይማኖታዊ በዓል ጳጉሜን 3 ቢከበርም ቀደም ሲል በነበረው ጊዜ ዓባይ ወንዝ ዳር ላይ ከጳጉሜን የመጀመሪያዋ ቀን ጀምሮ እስከ አዲስ ዓመት ዋዜማ ድረስ ከተለያዩ አካባቢዎች በተሰባሰቡ ሰዎች በተለያዩ የክዋኔ ሥርዓቶች ይከበር ነበር ነው ያሉት።
በዛሬው ዕለትም በበዓሉ መከበሪያ ቦታ (ዓባይ በረሀ ወንዝ ላይ) አካባቢ ተገኝተው በዓሉን እንዳከበሩም ገልጸውልናል። እንደቀደመው ጊዜ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ እንግዶች ባይታደሙም በአካባቢው በሚኖሩ ሰዎች በዓሉ እየተከበረ እንደኾነ መመልከታቸውን ነግረውናል።
የበዓል አከባበር ሥርዓቱ ከአማራ ክልል የሚሄዱት ድልድዩን ተሻግረው በኦሮሚያ ክልል፤ ከኦሮሚያ ክልል የሚመጡት ደግሞ ወደ አማራ ክልል በመሻገር የጥምቀት ሥነ ሥርዓቱን ያከናውናሉ ነው ያሉት ኀላፊዋ። ይህ የቆየ ሥነ ሥርዓት አሁንም ድረስ በበዓሉ አክባሪዎች ዘንድ በፍቅር እና በአንድነት የሚተገበር መኾኑን ኀላፊዋ ተናግረዋል።
በሁለቱም አቅጣጫ ወደ ቦታው ያቀኑ ጠበልተኞች መሐል ድልድዩ ላይ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ በተቃራኒው አቅጣጫ ተጉዞው የሚያከናውኑት የጥምቀት ሥነ ሥርዓት በየአካባቢው ማኅበረሰብ ጭፈራ እና ዝማሬ የታጀበ እንደኾነም ገልጸዋል። በዓሉ የእንኳን አደረሳችሁ መባባያ ከመኾኑም ባለፈ ከጥንት አባቶች ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉትም ተናግረዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዎች ቀደም ባሉት ዓመታቶች በበዓሉ አከባበር ላይ ተገኝተው ቦታው ላይ ፈጣሪ ዓመቱን በሰላም እንዲያደርሳቸው ተስለው ከነበር ስለታቸውን ይዘው እንደሚገኙም ገልጸዋል። የሚሳሏቸው ስለቶችም ድፎ ዳቦ፣ በሬ፣ በግ፣ ዶሮ እና ሌሎችም ሊኾን ይችላል ብለዋል።
ከዛም የእንስሳት እርድ ተፈጽሞ ከተዘጋጀ በኋላ እየተበላ እና እየተጠጣ ጨዋታው ይደምቃል ነው ያሉት። በዚህ ጊዜ “ዓባይን ያላየ ቀረ እንደ’ወለየ” እየተባለ ግጥም እየወረደ ይዜማል ነው ያሉት። ተነፋፍቀው የከረሙ ሰዎች የሆድ የሆዳቸውን ያወራሉ ብለዋል።
በበዓሉ የግብይት እና ሥራ ፈጠራ ተግባራት በጥቂት ቀንም ቢኾን አለ ያሉት ኀላፊዋ በበዓሉ ተዋውቀው ዝምድና የፈጠሩ ብዙ ሰዎች መኖራቸውንም ገልጸውልናል።
ሁለቱ ሕዝቦች ዓባይ ላይ በኅብረት በመዋኘትም ፈጣሪ ዓመቱን ካደረሰን ብለው ተስለው እና ተመራርቀው ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ፤ ዓባይን በእቃ በመጨለፍ እና እንደ ፀበል በመቁጠርም ውኃውን ወደ ቤታቸው ይዘው ይመለሳሉ ነው ያሉት። በዚህም ረድኤት በረከተ እንደሚያገኙ የሚያስቡ መሆኑንም ገልጸውልናል።
በፊት ላይ በዚህ የበዓል ክዋኔ ለመሳተፍ ከተለያየ አካባቢ ተነስተው ወደ ቦታው በሚያቀኑ ሰዎች ምክንያት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ ተሽከርካሪዎች እጥረት ገጥሞ ሰዎች በእግራቸው ተጉዘው እና በጭነት መጫኛ ተሽከርካሪዎች ወደ ቦታው የሚጓዙበት ሁኔታ እንደነበርም አውስተዋል።
ሁለቱ ማኅበረሰቦች ዘንድሮም እንደቀደመው ጊዜ በዓሉን በጋራ እንዳከበሩ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበኩታ ገጠም የለማ የሰንዴ ሰብል ልማት ተጎበኘ።
Next article“የጀመርናቸውን በመጨረስ፣ ያለምናቸውንም በመጀመር የኢትዮጵያን እመርታ ለማብሰር እየሠራን ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው