
ደብረ ማርቆስ: ጳጉሜን 3/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር እንስሳት ሃብት ልማት መምሪያ የእንስሳት ተዋፅዖ ምርቶችን በስፋት ለማቅረብ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጿል።
መምሪያው በከተማ አሥተዳደሩ ለማኅበረሰቡ ለዕርድ የሚኾኑ እንስሳት፣ የስጋ ደሮ እና እንቁላል ለገበያ ለማቅረብ ሢሠራ መቆየቱን የከተማ አሥተዳደሩ እንስሳት ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ በልስቲ ሹመት (ዶ.ር) ተናግረዋል፡፡
ጥራቱን የጠበቀ የወተት ተዋፅዖ ለተጠቃሚው ተደራሽ ለማድረግ ወተት እና የወተት ተዋፅዖ የሚሸጥባቸውን ቦታዎች በማስፋፋት ላይ መኾኑንም አብራርተዋል።
ለመጭው የዘመን መለወጫ በዓል የእንስሳት ምርት እጥረት እንዳይከሰት ሰፊ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ኀላፊው በተለይ የሥጋ ዶሮ፣ እንቁላል እና የወተት ተዋፅዖ ውጤቶችን በተደራጁ ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ለማኅበረሰቡ በማቅረብ የከተማው ነዋሪ ምርቱን በቅርበት እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ በቀን እስከ 90 ሺህ ሊትር የሚሠበሠበውን ወተት በጥራት እንዲያቀርቡ ለማኅበራት ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት 230 ሺህ የአንድ ቀን ጫጩት ለማስገባት ታቅዶ 468 ሺህ በማቅረብ ለበርካቶች የሥራ ዕድል እየተፈጠረላቸው ይገኛል ነው ያሉት።
መምሪያ ኀላፊው የአንድ ቀን ጫጩት በወቅቱ ለማምጣት በወረፋ ምክንያት እያጋጠመ ያለውን መዘግየት በዘላቂነት ለመፍታት ባለሃብቶችን በማሳተፍ የጫጩት ማስፈልፈል ሥራ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
በእንስሳት ልማት ሥራ ተሰማርተው እየሠሩ ያሉ የከተማው የማኅበረሰብ ክፍሎችም ውጤታማ እንዳደረጋቸው ለአሚኮ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን