
ጎንደር: ጳጉሜን 3/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ”እመርታ ለዘላቂ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት የእመርታ ቀን በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በፓናል ውይይት ተከብሯል።
በመድረኩ የከተማ አሥተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ነዋሪዎች እና በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ተገኝተዋል።
እንደ ሀገር የግብርና ዘርፉን በተገቢው መንገድ በመደገፍ ምርታማነትን ለማሳደግ በተሠራው ሥራ ውጤት መመዝገቡን ያነሱት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ አበራ አደባ ለዚህም የበጋ መስኖ ስንዴ፣ የሌማት ትሩፋት እና ሌሎችም ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።
ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አቶ አበራ አደባ አንስተዋል።
ጎንደር ለኢንቨስትመንት ምቹ እና ተመራጭ ከተማ መኾኗን ያነሱት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ የኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ ፋሲል ዘውዱ ናቸው።
ዘርፉ በከተማዋ የሥራ ዕድል መፍጠርን ጨምሮ የከተማዋን ዕድገት እያፋጠነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ከ3 ሺህ በላይ የከተማዋ ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ያነሱት አቶ ፋሲል የአገልግሎት ዘርፉም ለከተማዋ ዕድገት መሠረት እየጣለ መኾኑን አመላክተዋል።
እንደ ሀገር የግብርና እና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ለውጥ እንዲያመጣ መንግሥት በትኩረት መሥራት እንዳለበት የመድረኩ ተሳታፊ ኢንቨስተሮች ጠቁመዋል።
የማኅበረሰቡን ኑሮ ሊያሻሽሉ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባም በውይይቱ የተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎች አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ደስታ ካሳ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን